Author Topic: የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ? (ሐምሌ 24-ነሐሴ 1፣ 2003)  (Read 3645 times)

staff2

  • Administrator
  • Newbie
  • *****
  • Posts: 597

የአገር ቤት ጋዜጦች ምን ጻፉ? (ሐምሌ 24-ነሐሴ 1፣ 2003)

የኦብኮው ሰው መጨረሻ
—–

ሀብታም እና ድሃ ባለሥልጣኖቻችን ሊታወቁ ነው?
—–

መኢአድ ሰላም ርቆታል
—–

በመጪው ዓመት ለግል ሬዲዮና ቲቪ ጣቢያ ፈቃድ አይሰጥም
—–የኦብኮው ሰው መጨረሻ

ዶ/ር መረራ ጉዲና የመሰረቱት የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ በምርጫ 97 ማግስት ለሁለት ተከፈለ ተባለ። አይዞህ ባይ እንዳላቸው ንግግራቸው ያሳብቅባቸው የነበሩት የኦሕኮ የፓርላማ ተመራጭ፣ የአሁኑ የኦብኮ መሪ አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ “ኦብኮ” የሚለውን ስም ወርሰው ድንገት የፓርቲ መሪ ሆነው ብቅ አሉ። እነዶ/ር መረራም ሌላ “ኦሕኮ” የሚል አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ተገደዱ። አቶ ቶሎሳ ዛሬ ፖሊስ የሚፈልጋቸው፣ ፍርድ ቤት ከአገር እንዳይወጡ ያዘዘባቸው፣ መያዣ የቆረጠባቸው ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ናቸው። አቶ ቶሎሳ ከግብራበራቸው ከአቶ ቦና ጋራ በከባድ የማጭበርበር ወንጀል ተከሰዋል። ባለፈው ሳምንት እቤታቸው በሄዱ ፖሊሶች ላይ ሽጉጥ መዝዘው በጓሮ በር እንዳመለጡ እስካሁን ዱካቸው አልተገኘም። የፓርላማ አባል በነበሩበት ወቅት “መሬት አሰጣችኋለሁ” በማለት ከ15 ተበዳዮች ከ900 መቶ ሺህ ብር በላይ ተቀብለዋል ተብሏል። ዓቃቤ ሕግ የማስረጃ እጥረት የለም ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቦታል።
“አቶ ቶሎሳን ኢሕአዴግ ከዳቸው”ሲሉ ወዳጆቻቸው አዝነውላቸዋል። “የቶሎሳ ኦሕኮ አገልግሎቱን ጨረሰ ማለት ነው?” ሲሉም የ4 ኪሎ ጓደኞቻቸው ገና ከአሁኑ ሐሜት ጀምረዋል። “እሱም አበዛው” ያሏቸውም አሉ።

—–

ሀብታም እና ድሃ ባለሥልጣኖቻችን ሊታወቁ ነው? መቼ?!

የጸረሙስና ኮሚሽን ከ17 ሺህ የሚበልጡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የምክር ቤት ተመራጮችን፣ ተሿሚዎችን፣ የሥራ ሐላፊዎችንንና ሠራተኞችን ሀብት መመዝገቡን ገልጿል። የተመዘገበው ሀብት ዝርዝርና መጠን ትክክለኛነት ከተረጋገጠ በኋላ የመንግሥት ባለሥልጣናቱና ሠራተኞች መረጃ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል ተብሏል። ከ1200 የሚበልጡ የመከላከያ ሚኒስቴር ሐላፊዎች፣ የጉምሩክ ሐላፊዎችና ሠራተኞች ይገኙበታል። የመንግሥት የንግድ ድርጅቶችን በተለያየ ደረጃ የሚመሩ 4200፣ 600 ይጠጋሉ የተባሉ የፌዴራል ፖሊስ ሰዎች፣ 170 ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ 120 የፌዴራል ፍ/ቤት ዳኞች፣ 25 አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ሀብት አስመዝግበዋል። በጣም ሀብታሙንና በጣም ድሐውን የመንግሥት ባለስልጣን ለማወቅ ሕዝቡ በጉጉት ይጠብቃል። ውጤቱ ይፋ እስከሚሆን በግምት እንቆያለን። በጣም ድሃው የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣን ማን ይመስልዎታል? በጣም ሀብታሙ የክልል ፕሬዚዳንትስ? ሀብታም የፓርማ አባልነትንስ ማን ይወስዳል?
“አዲስ አድማስ” ጋዜጣና “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ዘግበውታል
—–

የመኢአድ ም/ሊቀመንበር እና የኢሶዴፓ ሊቀመንበር ከሐላፊነታቸው ተነሱ

መኢአድ ሰላም ርቆታል። ም/ፕሬዚዳንቱ አቶ ያዕቆብ ልኬ ባለፈው ሳምንት “ነገሩ ወሬ ነው” ቢሉም በዚህ ሳምንት ከሥልጣናቸው መነሣታቸው እውነት ሆኗል፤ ነጋድራስ ጋዜጣ እንደዘገበው። የሰውየው ድክመት “ከሥራ ባለደረቦቻቸው ጋራ ተግባብተው አለመሥራት፣ ሁሉንም እኔ አውቃለሁ ማለት፣ የፓርቲውን ሥራ አስተባብረው ለመሥራት አለመቻል፣ ሌሎችን ዝቅ አድርጎ መመልከት እና ችኩልት” ነው መባሉን “ነጋድራስ” ከትቧል። የአቶ ያዕቆብ መጨረሻ በቅርቡ ይጠራል በተባለው የድርጅቱ ምክር ቤት ጉባኤ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛል ተብሏል።
“ፍትሕ” ጋዜጣ እንደዘገበው እነኢንጂነር ኀይሉ ሻውል ቢሯቸውን ታግዶ ለነበረው የእነአቶ ማሙሸት አማረ ቡድን እንዲያስረክቡ ፍርድ ቤት አዟቸዋል። ይህን ትእዛዝ ባለማክበራቸውም በፖሊስ ተይዘው እንዲቀርቡና እንዲያስረዱ ታዞባቸዋል። ይህን ተከትሎ ዐርብ እለት ቢሮውን ለመረከብ በተገኙት የእነአቶ ማሙሸት ቡድን አባለትና በሌላው ወደን መካከል በፓርቲው ጽ/ቤት “የጦፈ ድብድብ” መጀመሩን አዲስ አድማስ ዘግቧል። ፖሊስ የፍርድ ቤት ትእዛዝ ተግባራዊ እንዳይሆን አድርገዋል ያለቸውን በድብድቡ የተሳተፉ ሰዎችን አስሯል ተብሏል። አቶ ማሙሸት ቢሯቸውን ከተረከቡ በኋላ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ሲናገሩ “አሁን ጽ/ቤታችን ገብተናል፤ ቦታችንን አቶ ኀይሉ በስጦታ የሰጧቸው ሰዎች እንዲያስረክቡን አንጠይቅም፤ አናቃቸውም” ብለዋል። ለኢ/ር ኅይሉ ባስተላለፉት መልእክትም “ወደ ሕሊናው ተመልሶ የሐሰት አሉባልታ ወሬውን መስማት አቁሞ እውነቱን ተረድቶ የላዕላይ ም/ቤት ካልጠራ እኛ ጠርተን የፓርቲውን ሕልውና እናረጋግጣለን” ብለዋል። በመጨረሻ ግን በኢ/ር ኀይሉ የሚመራው የሥራ አስፈጻሚ ቡድን ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤት በማለታቸው እነአቶ ማሙሸትን ወደ ቢሯቸው ያስገባቸው የስር ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ እስከ ጥቅምት 16፣ 2004 ታግዶ እንዲቆይ ተወስኗል።
ሰሞኑን በተከታታይ የሚወጡት ዘገባዎች በእነአቶ ማሙሸት እና በእነኢንጂነር ኀይሉ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት በጣም እንደተካረረ ይጠቁማሉ።
በተመሳሳይም ከኢሕአዴግ “አጋር”ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀ መንበር አቶ አብዱል ፈታህ አብዱላሂ “በአቅም ችግር” ከሐላፊነታቸው መነሣታቸውን “ሰንደቅ” ጋዜጣ አስነብቧል። የፌዴራሉ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አብዱል ፈታህ ከሚኒስትርነታቸው ይነሱ አይነሱ የተባለ ነገር የለም። በተለመደው የኢሕአዴግ አሠራር ግን ፓርቲው በአቅም ማነስም ይሁን በሌላ የገመገመው ሰው ከፓርቲው ቢነሣም በመንግሥት ሐላፊነቱ አይወርድም፣ ወይም ተጨማሪ ሹመት ይሰጠዋል።
——

በመጪው ዓመት ለግል ሬዲዮና ቲቪ ጣቢያ ፈቃድ አይሰጥም

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በመጪው ዓመት ለአዲስ የግል ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ ፈቃድ ለመስጠት እቅድ እንደሌለው ገልጿል፤ “የሰጠኋችሁ ይበቃችኋል” ይመስላል፤ ወይም ፈቃድ መስጠት ደክሞት ይሆናል። “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ በፊት ገጹ እንደዘገበው የባለሥልታኑ አንድ ሐላፊ በ2003 ለግል ሬዲዮና ቴሌቪዥን ፈቃድ የጠየቀ የለም። ስለዚህ መሥሪያ ቤታቸው በመጪው ዓመት የሬዲዮና ቲቪ ፈቃድ ጠያቂዎች ቢመጡ እንኳን “ፈቃድ የመስጠት እቅድ የለውም።” በተገባደደው ዓመት ለ11 ጋዜጦች እና ለ31 መጽሔቶች የምዝገባ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል። በህትመት ሚዲያ ዘርፍ “ፈቃድ ጠይቆ የተከለከለ የለም” ሲሉም ሐላፊው አቶ ሙሉጌታ ሲሳይ “ዐይኔን ግንባር ያርገው” ብለዋል።
ጋዜጣው በአሁኑ ወቅት ስንት የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዳሉ፣ ስንቱ በመንግሥትና በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ፣ ፈቃድ ከተሰጣቸው ጋዜጦችና መጽሔቶች ስንቶቹ ስራ ላይ እንደሚገኙ ወይም በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ ወዘተ. የጠቀሰው ነገር የለም።
—–

ነጋዴዎች “ፋይላችሁ ጠፍቷል” እየተባሉ ለእንግልት ተዳረጉ

አዲስ አድማስ ጋዜጣ በቅዳሜ እቱሙ እንዳለው በፌዴራል ንግድና ኢንዱስትሪ ዳግም ምዝገባ ለማድረግ የተሰለፉ ነጋዴዎች “ፋይላችሁ ጠፍቷል” በመባላቸው ሊስተናገዱ አልቻሉም። የሚኒስቴሩ ንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ግን “ነጋዴው በመጨረሻ በአንድ ጊዜ በመምጣቱ መጨናነቅ ተፈጥሮ እንጂ የምንም ፋይል አልጠፋም” ብለዋል፣ ለጋዜጠው።
—–

ቻይናውያን በኢትዮጵአ 1168 ፕሮጀክቶች አሏቸው

ቻይናውያን ገና ወደ ኢትዮጵያ አልገቡም የሚል ካለ ተሸውዷል። መንገድና ድልድይ በመስራት ብቻ የቆሙ የሚመስለው ካለ እሱ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖረ አይደለም። የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ቻይናውያን 1168 የተመዘገቡ ፕሮጀክቶች/ፈቃዶች በኢትዮጵያ እንዳላቸው አስታውቋል። ስራ የጀመሩት ግን 370 ብቻ ናቸው። “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ነው ነገሩን የዘገበው። ቀሪዎቹ ቻይናዎች ምን እያደረጉ ነው? ምናልባት አማርኛ እያጠኑ፣ እስክስታ እየለማመዱ ይሆናል። እንደዚያም ሆኖ ግን ፈቃድ ከወሰዱት የሚበዙት በማኑፋክቸሪንግ እና በግብረና መስክ ለመሰማራት እንደሚፈልጉ መግለጫው ያስረዳል። እስከአሁን በሥራ ላይ የተሰማሩት ቻይናውያን 44 ቢሊዮን ብር ገደማ ካፒታል አስመዝግበዋል ተብሏል።
—–

ሼኹ በሙሉ ገጽ

“ሰንደቅ” ጋዜጣ የረቡዕ ዕለት እትሙን የፊት ገጽ ለሼኽ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲ ፎቶና ዜና ሰውቷል። መሐመድ አልአሙዲ በስተቀኝ ጎናቸው ፈገግ ሲሉ ያሳያል የጋዜጣውን የፊት ገጽ የግራ ጠርዝ የሞላው ፎቶ። በገጹ መካከልም ይህ ርእስ ተጽፏል፤”የኢትዮ-ሪቪው ድረገጽ ባለቤት ኤሊያስ ክፍሌ በስም ማጥፋት ወንጀል 175 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ተወሰነበት።” ነገሩን ቀደም ብሎ ለማያውቅ ሰው በተለየ ትልቅ መጠን የተጻፈው “175 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ተወሰነበት” የሚለው የርእሱ ክፍል ሼኹ የተፈረደባቸው መስሎት ሊደነግጥ ይችላል። ቢቢሲን ዋቢ አድርጌያለሁ ያለው ጋዜጣው ዜናውን እንዲህ ሲል ጀምሯል። “ተቀማጭነቱ በዩናትድ ስቴትስ አሜሪካ የሆነው ኢትዮ-ሪቪው ድረ ገጽን በመጠቀም በክቡር ዶ/ር ሼኽ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ ስም የማጥፋት ድሑፍ አትሞ በማሰራጨቱ ምክንያት በለንደን ፍ/ቤት የተከሰሰው አቶ ኤልያስ ክፍሌ 175 ሺህ ዶላር ቅጣት ሰሞኑን ተበየነበት። ቅጣቱ የተጣለው አቶ ኤልያስ ክፍሌ ከኤርትራ መንግሥት በተሰጠው ተልዕኮ በመነሳት፤ ዶ/ር ሼህ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲንን ለአሸባሪው የአልቃይዳ ቡድን የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ በማለት የሐሰት ውንጀላ በመሰንዘሩ በእንግሊዙ ፍርድ ቤት በመረጋገጡ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።”
ሼኹ በውሳኔው መደሰታቸውን “ቅርበት ያላቸው ምንጮች” እንዳረጋገጡለት የዘገበው “ሰንደቅ” አክሎ ሰውየው አንድ ወንድ እና ሰባት ሴት ልጆች እንዳሏቸው ተቅሷል። በክሱ ሒደት የአንዲት ሴት ልጃቸው ጉዳይ መነሣቱን ግን ሳይጠቅሰው ቀርቷል።
——

በአዲስ አበባ የአልጋ (ቤት) እጥረት አለ

“አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ነው አዲስ አበባ በአልጋ እጥረት መቸገሯን የጻፈው። ስለከተማዋ ፔኒሲዎኖች ዘለግ ያለ ጽሑፍ ቀርቧል። እንዲህ በማለት ራሱን ይዘጋል፤ ጽሑፉ። “በፔንሲዮኖች ውስጥ ፍቅር እንዳለ ሁሉ ስርቆሽም አለ። ቃል መግባት እንዳለ ሁሉ ቃል ማፍረስም አለ። በድብቅ የሚሠራ ሥራ ብዙዎችን ለትዳር መፍታትና ለተጨማሪ ማኅበራዊ ቀውስ ዳርጓቸውም ያውቃል። በዋናነት ግን የኤች አይ ቪ መስፋፋት መነሻዎችም ሊሆኑ ይችላሉ።…ብዙ ተማሪዎች ከሰውና ከቤተሰብ ለመሸሸግ አማራጭ ቦታም አድረገው ወስደውታል። የዚህ ዓይነት ቢዝነስ ማካሄድ ልክ ነው አይደለም የሚል መደምደሚያ ውስጥ መግባት ባንሻም አሁን በከተማው ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ይኸው ነው። ‘አገልግሎት መስጫ’ ቦታዎች እየተስፋፉ ነው። ነገር ግን አሁንም እጥረት አለ። ይህ ከፍተኛ የአልጋ ቡቶች ፍላጎት ለምን ተከሰተ? ምናልባት በጠቀስነውና ባልደረሰንበት ሌላ ምክንያት ሊሆን የሚችል ከሆነ ጥናት ሳያሻው አይቀርም።”
በጥቅምት ወር 2003 በአዲስ አበባ 712 ሆቴሎች፣ 323 ፔንሲዮኖች እና 69 ገስት ሐውሶች ተመዝግበዋል። 1104 አልጋ አገራዮች እንደማለት ነው። 1104 ምን አላት?! አልጋ ላይ የመውደቅ ጥንዳዊ ፍላጎት (የአልጋ ፍላጎት) ከኢኮኖሚ እድገቱ ጋራ ያለው ግንኙነት ቀጥተኛ ይሁን ተቃራኒ የተባለ ነገር የለም።

የአገር ቤት ምርቃት

“ማሐሙድ ጋ ጠብቂኝ” በመጽሐፍ ታተመ
“አዲስ አድማስ” ጋዜጣ
—–

የቀድሞው የዳሸን ቢራ ሥራ አስኪያጅ 18 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው
ሪፖርተር
—–

የደራሲ መስፍን ሀብተ ማርያም የሕጻናት መጽሐፍ ለንባብ በቃ
“አዲስ አድማስ” ጋዜጣ
—–
አንድነት “ፍኖተ ነጻነት” የተባለ ጋዜጣ ማሳተም ጀመረ
“ፍትሕ” ጋዜጣ
—–
ብርቱካን ሚደቅሳ የሬጋን-ፋሴል ዴሞክራሲ ፌሎውሺፕ አሸናፊ ሆነች፤ የሕይወት ታሪኳን ለመጻፍ ዝግጅቷን እንደጨረሰች ይፋ አደረገች
“ፍትሕ” ጋዜጣ
—–

የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ከሐላፊነታቸው ተነሱ
አዲስ አድማስ ጋዜጣ
—–
ፓትርያርኩ “ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና እና ሥርዓት ውጭ ‘እገሌ ተሐድሶ ነው’ ‘እገሌ መናፍቅ ነው’ የሚል እንቅስቃሴ ከሐምሌ 25 ቀን ጀምሮ ሕገ ወጥ መሆኑንና ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚካሄድበት አስታወቁ።
ሪፖርተር ጋዜጣ

የሳምንቱ ምርጥ አባባሎች

“ለእኔ አሁን ያለንበት ይህ ሥርዓት የነፍጠኛ ሥርዓት ነው።”
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ “ለእኔ ነፍጠኛ የግድ አማራ መሆን የለበትም። ኦሮሞም፣ ትግሬም ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ አይደለም ነፍጠኛ።… በነፍጥ የሚያስገድድ ሁሉ ነፍጠኛ ነው። ሕዝብን በማስገደድ በፈለገው መንገድ ለመምራት የሚሞክር ቡድን ለእኔ ነፍጠኛ ነው….” ሲሉ “አሁን ያለውን ሥርዓት ነበፍጠኝነት ይጠረጥሩታል” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ። “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት
« Last Edit: August 07, 2011, 03:24:32 PM by staff2 »