Author Topic: ከአራት አሥርታት ዓመታት በኋላ በሚያስገርም ሁኔታ ከእንቅልፉ የባነነው ኢሕዴን-ብአዴን-አዴፓ  (Read 4581 times)

staff3

  • Global Moderator
  • Newbie
  • *****
  • Posts: 260
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት               

ሓሙስ ሓምሌ ፳፭ ቀን ፪ሺህ፲፩ዓ.ም.      ቅጽ ፯ቁጥር ፲፪
----------------------------------------------------------------------
ከአራት አሥርታት ዓመታት በኋላ በሚያስገርም ሁኔታ
ከእንቅልፉ የባነነው ኢሕዴን-ብአዴን-አዴፓ
----------------------------------------------------------------------

በአሁኑ ወቅት የአማራ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (አዴፓ) ነኝ የሚለው የፖለቲካ ድርጅት አፈጣጠሩን፣ ማንነቱን፣ የትግል ሕይወቱን እና ዓላማውን ለማወቅ ፈጣሪውን፤ አያቱን እና አባቱን ማን እንደሆኑ ማወቅ የግድ ይላል። የአዴፓ አባት ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሲሆን፤ አያቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) ነው። ኢሕዴንን በአካሉና በአምሳሉ ጠፍጥፎና ቀርጾ የፈጠረው ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትሕነግ)/ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ነው። ስለዚህ፣ ትሕነግ/ሕወሓት የአዴፓ ቅድመ-አያት ነው። ለዚህ ነው፣ ትሕነግ/ሕወሓት ፈጣሪው ነው የምንለው። በዚሁ አኳያ፤ የአባቶቻችን አባባል በመውሰድ “ውሃን ከምንጩ፤ ነገርን ከሥሩ” ነውና፤ ወደ ኋላ ሂደን ኢሕዴን-ብአዴን-አዴፓ የተጓዘበትን የ40 ዓመታት (12 ዓመት እንደ ኢሕዴን፤ 28 ዓመት ደግሞ እንደ ብአዴን)  የፖለቲካ ትግል ታሪኩን በመጠኑ በመዳሰስ እውነተኛ ማንነቱ ለማወቅ እንችላለን።

1.     የኢሕዴን አመሠራረት

በ1971/72 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር(እ.ኢ.አ.)  ጎንደር ከፍለ-ሃገር በበለሳ ወረዳ አካባቢ፣  ይንቀሳቀስ ከነበረው በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የሚመራው የፓርቲ ወታደራዊ ክንፍ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት  (ኢሕአሠ) አባል የነበሩ ወደ 36 የሚጠጉ ክድተው ወደ ትግራይ ክፍለ-ሃገር በመሄድ ለትሕነግ/ሕወሓት እጃቸውን ሰጡ። ይኸን ተገንጣይ አንጃ ትሕነግ/ሕወሓት በአካሉና በአምሳሉ ጠፍጥፎ ፈጥሮ ኢሕዴን የሚል መጠሪያ ስም ሰጥቶ ህዳር 11 ቀን 1973 ዓ/ም እ.ኢ.አ. በትግራይ በርሃ ውስጥ ፈጠረው።

ኢሕዴን የፈጣሪውን ትሕነግ/ሕወሓት ፖለቲካ ዓላማ ተጠመቆ፤ ፈጣሪው በጠመቀው ፖለቲካ ዓላማ እና መንፈስ ታንጾ የተቋቋመ፤ በውጫዊ ገጽታው ኢትዮጵያዊነት የተላበሰ የሚመስል ሆኖም ግን በውስጣዊ ይዞታው የትሕነግ/ሕወሓት ውላጅ የሆነ ነው። በዚሁ መሠረት፣ ፈጣሪው ትሕነግ/ሕወሓት ያጠመቀው ሶስት (3) አበይት የፖለቲካ ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፥

1ኛ/ ኤርትራ በኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ሥር የምትገኝ ሃገር ናት። የኤርትራ ሕዝብ ለነጻነት የሚያደርገውን ትግል        በማንኛውም መስክ መደገፍ፣ ማገዝ፤

2ኛ/ ኢትዮጵያ የብሔረስቦች እስር ቤት ናት። አስሮ የያዛቸውም “ጨቋኙ” የዐማራ ነገድ ነው። ዐማራም ቀንደኛ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነው። ስለዚህ፣ ይኸ የዐማራ ነገድ መጥፋት አለበት።

3ኛ/ “የጨቋኙ” የዐማራ ነገድ ዋና መጨቆኛ መሳሪያ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ስለሆነ የዐማራውን ነገድ ከስር ነቅሎ ለማጥፋት የኦርቶዶክስን እምነት መሰረት በመናድ ማክሰም  ናቸው።

እንግዲህ ኢሕዴን እነዚህን አበይት ሶሰት (3 ) ዓላማዎች በድብቅ አንግቦ ነበር፤ የትጥቅና የፖለቲካ ትግሉን በወሎ፣ በጎንደር በኋላም በጎጃምና በሽዋ ማስፋፋት የያዘው። በዚሁ የትጥቅ ትግል ወቅት የትሕነግ/ሕወሓት ታጋዮች የኢሕዴን ታጋዮች “ዱቄት ተሸካሚ” “አሽከር” እያሉ ይጠሯቸው ነበር። ኢሕዴን ሕብረ-ብሔር ድርጅት ሆኖ ሲመሠረት አብዛኛው መሪዎቹ የኤርትራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሞ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ተወላጆች ነበሩ። የድርጅቱ ቋንቋ “የጨቋኙ” ዐማራ ነገድ ቋንቋ አማርኛ ነበር/ ነው። በዚህ የተነሳ፤ ኢሕዴን የትሕነግ/ሕወሓትን ዓላማ ማስፈጸሚያ በመሆኑ የትሕነግ/ሕወሓት የአማርኛ ተናጋሪ ክንፍ ይባል ነበር።

ትሕነግ/ሕወሓት እና ኢሕዴን በጋራ በመሆን የኢትዮጵያ “ሕዝቦች” አብዮታዊ ዴሞከራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ግንቦት 1980 ዓ/ም እ.ኢ.አ. መሠረቱ። ትሕነግ/ሕወሓት እንደ ጌታ ኢሕዴን ደግሞ እንደ ሎሌ (አሽከር) ሆነው ከደርግ ጋር መጠነ ሰፊ ጦርነቶች አካሂደው እና በለስ ቀንቷቸው እ.ኢ.አ በግንቦት 1983 ዓ/ም በተረ-መንግሥቱ በጠበጃ ኃይል ያዙ።

2.    የብአዴን አመሠራረት

በኢሕአዴግ ሽፋን ሥልጣን ላይ የወጣው ፀረ-ዐማራው ትሕነግ/ሕወሓት፤ ሥልጣን በወጣ ማግስት በዐማራው ሕዝብ ላይ ስውር ጦርነት በማወጅ በአሩሲ፣ በሐረር እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች ያካሄደው መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋና ማፈናቀል ዘመቻ ለመቋቋምና ለዓለም ህብረተሰብ ለማሳወቅ በታላቁ መሪያችን ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ሰብሳቢነት የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) በ1984 ዓ/ም እ.ኢ.አ. ተቋቋመ። ለታፈነው ዐማራ ሕዝብ ድምጽ መሆን ሲጀመር፤ ይኸን ለመቋቋም ሲባል ትሕነግ/ሕወሓት አሽከሩን እና ሎሌው የሆነውን ሕብረ-ብሔር ድርጅት- ኢሕዴንን- በአንድ ጀንበር ውስጥ ወደ ዐማራ ነገድ ድርጅት በመቀየር  ከኢሕዴን ወደ “ብሔረ” ዐማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) እ.ኢ.አ በ1985 ዓ/ም ቀየረው።

በኢሕዴን ውስጥ በመሪነት የነበሩት አማርኛ ተናጋሪ ኤርትራውያን፣ ትግሬዎች፣ ኦሮሞዎች እና የደቡብ ኢትዮጵያ ተወላጆች የብአዴንን አመራርነት በመቀበል የምድር ሲዖል የሚያየውን ዐማራ ሕዝብ በዐማራ “ክልል” ተብየውና በፌዴራል መንግሥት መዋቅር ላይ ስልጣን በመያዝ መምራት ጀመሩ።

በመሪነት የነበሩ የዐማራ ተወላጆች እንደ ሙሉዓለም አበበ እና ሌሎችም ዐማራ ያልሆኑ የሌላ ብሔር ተወላጆች ዐማራ የሆነ ድርጅት መምራት አይችሉም፤ ብአዴን በተወካይ አይመራም፣ ቦታቸውን ይፈልጉ የሚል ውስጣዊ ትግል ቢያደርጉም፤ ትሕነግ/ሕወሓት የሰገሰጋቸው ቅጥረኞች እንደ በረከት ስምዖን (ኤርትራዊ)፣ ካሣ ተክለብርሃን (ትግሬ)፣ ሕላዊ ዮሴፍ (ትግሬ)፣ አዲሱ ለገሰ (ኤርትራዊና ኦሮሞ)፣ ተፈራ ዋልዋል (ሲዳማ)፣ ታደሰ ካሣ (ትግሬ)፣ ተሰማ ገብርሕይወት (ትግሬ)ወዘተ... የመሳሰሉት አንድ በአንድ የዐማራ ተወላጆችን በረቀቀ ሴራ እየመነጠሩ አጠፏቸው። እነዚህ የለየላቸው ፀረ፟-ዐማራ አመራሮች የዐማራውን ሕዝብ ቋንቋ በመናገራቸው ብቻ ዐማራ መስለው በመታየት ፤ በፈጣሪያቸው ትሕነግ/ሕወሓት ትዕዛዝ በዐማራው ሕዝብ ላይ ባለፉት 28 ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ለሕሊና በሚዘገንን ሁኔታ ከድህነት ወለል በታች ውስጥ ዘፈቁት። በትንሹ ለመጥቀስ ያህል፥

1ኛ/ ዐማራውን ያገለለውን እና በቁሙ የቀበረውን የትሕነግ/ሕወሓትን አግላይ ሕገ-መንግሥት በዐማራው ላይ ጫኑበት፤

2ኛ/ የዐማራው ሕዝብ አጽመ-ርስት የሆኑትን መተከል፣ ወልቃይት. ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ራያ፣ ቆቦ፣ አለማጣ፣ ደራ ወዘተ.. እንዲነጠቅ አደረጉ፤

3ኛ/ በትሕነግ/ሕወሓት መሪነት በዐማራ ላይ የዘር ማጽዳት (ethnic cleansing) እና የዘር ጭፍጨፋ (genocide)  ሲካሄድበት በእጅ አዙር የድርጊቱ ተባባሪዎች ሆነው አስጠቁት፤

4ኛ/ በርካታ የዐማራው የቁርጥ ቀን  ልጆች የሆኑትን ፕ/ር አስራት ወልደየስ እና ተከታዮቻቸውን የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅትን(መዐሕድ) መስርተው በዐማራው ህልውና ላይ የተጋረጠውን መጠነ ሰፊ አደጋ ለመቋቋም የተጀመረውን ትግል በመምራታቸው የዚሁ ግፍ ቀማሽ ሆነው የሕይወት መስዋእትነትን አንዲከፍሉ ተደረገ፤

5ኛ/ ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ስብራት ለማድረስ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በማፍሰስ ሰፊ የሆነ ዐማራውን ጥላሸት የመቀባት ፕሮፓጋንዳና ልብ ወለድ ሃታታ በተከታታይነት ተስርቷል፤

6ኛ/ ለከፍተኛ የማህበራዊ ችግሮች፤ ሴቶቻችንን በማምከን፤አብዛኛው ዐማራ ደግሞ ለኮሌራ ና ተስቦ በሽታዎች፤ እንዲጋለጥ ሆኖ በኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ እንዲማቅቅ አደረጉት፤

7ኛ/ በተለያዩ ቦታዎች ዐማራው ሲጨፈጨፍ፣ ሲፈናቀል፣ ሃብትና ንብረቱ ሲቃጠል፣ ወደ ሃገርህ ሂድ ሲባል፣ ከሞት የተረፈው እርዳታ ለማግኘት ወደ ዐማራ “ክልል” ሲመጣ ወደ መጣህበት ተመለስ እየተባለ በግፍ ላይ ግፍ ፈጸሙበት፤ አሁንም አላቆመም። ከሁሉም በላይ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ክ1972 እስከ ፳፲፩፯ ዓ.ም እ.ኢ.አ የትግሬ ወያኔ የአፓርታይድ አገዛዝ በዐማራ ነገድ ላይ ሆን ብሎ ፤ አቅዶና አስቦ የፈጸመውን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት  ወንጀል በስነድ በፎቶግራፍ፤በቃለመጠይቅ በሰዎች ምስክርነት በቦታ ከወንጅሉ ሰለባዋች ማንነት ጋር አበጥሮ “ ም ጽ አ ተ ዐማራ ፦ ተገድሎና ተገዳድሎ የማያልቅ፤ ተነቅሎ የማይደርቅ” በተሰኘው ደጎስ ያለ መጽሃፉ ለሕዝብ አቅርቦታል፡|፡ አሁንም የዐማራው እልቂትና ፍጅት እንደቀጠለ ነው፡፤

አንድ የዐማራ ተወላጅ የብአዴን አባል ሆኖ ሲመለመል ዋናው መመዘኛው እንደ አንደኛ ደረጃ የፖለቲካ እምነት መቀበልና በጽኑ ማመን ያለበት ዐማራ “ጨቋኝ” ነገድ መሆኑን ተቀብሎ በተግባር ማሳየት አለበት። ስለዚህ ነው፣ ይህ ሁሉ ጭፍጨፋና መፈናቀል በትሕነግ/ሕወሓት አቀናባሪነት እና መሪነት በዐማራው ላይ ሲፈጸም፤ ብአዴን ለግፉ ተባባሪ የሚሆነው።

3.    የአዴፓ አመሠራረት

የትሕነግ/ሕወሓት ቅኝ አገዛዝ ያንገፈገፈው የዐማራ ሕዝብና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ዳር እስከ ዳር ድረስ ከፍተኛ ሕዝባዊ  መሬት አንቀጥቀጥ አመጽ  እ.ኢ.አ. ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች ባካሄዱበት ወቅት፤ ሥር-ነቀል ለውጥ አምጥቶ ትሕነግ/ሕወሓት ከተላላኪ ድርጅቶቹ ጋር ወደ ማይቀረው ከርሰ መቃብራቸው ለማውረድ በተቃረበበት ጊዜ፤ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች በሸረቡት ከፍተኛ የፖለቲካ ሴራ፥

1ኛ/ ትሕነግ/ሕወሓት 27 ዓማታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በስራው ወንጀሎችና በዘረፈው ሃበት ላይጠየቅ መንበረ-ሥልጣኑን ለቅቆ ወደ ክልሉ ትግራይ ጓዙን ጠቅልሎ እንዲሄድ፤

2ኛ/ ሥርዓቱን ጠጋግኖ እድሜውን  ለማራዘም  የኦሕዴድን አባል የኢሕአዴግ ሊቀመንበር እና የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ እንዲመረጥ በተደረገው ከፍተኛ የፖለቲካ ሴራ የትሕነግ/ሕወሓት ውርስ ወይም ውላጅ የሆነው ዶ/ር ኮሎኔል አብይ አህመድ መንበረ-ሥልጣኑን እንዲይዝ፤ ተደረገ።

ሴራው ግቡን መትቶ፤ ትሕነግ/ሕወሓት ጓዙን ይዞ ትግራይ መሸገ፤ ዶ/ር ኮሎኔል አብይ አህመድ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ሊቀመንበር በመሆን የጠቅላይ ሚንስተሩን ቦታ ያዙ። ኦሕዴድ በብልጣብልጡ ዶ/ር ኮሎኔል አብይ አህመድ እየተመራ የመንግሥቱን መዋቅሮች በራሱ ድርጅት አባላት እየሰገሰገ ታይቶ እና ተሰምቶ በማይታወቅ ፍጥነት ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከትሕነግ/ሕወሓት የትግራይ ቅኝ ግዛትነት ወደ የኦሕዴድ ኦሮሞ ቅኝ ግዛትነት አሸጋገሯት። ግለስብ አሻጋሪ ክቶውንም ሊሆን እንደማይችል እየታወቀ ዶ/ር ኮሎኔል አብይ አህመድ “እመኑኝ እኔ አሻግራችኋለሁ” ያሉት ትርኢት እውነቱ  ይኸው ነው።

ይህ በዚህ እንዳለ፤ ኢሕዴን-ብአዴን ደግሞ እንደልማዱ የሎሌነት ሽግግር እደረገ። ከትሕነግ/ሕወሓት ሎሌነት ወደ ኦሕዴድ ገረድነት ተሸጋገረ። ጌታው ኦሕዴድ ስሙን ቀይሮ ወደ ኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) ሲቀይር፤ ብአዴን የጌታውን ፈለግ በመከተል በዐማራ ሕዝብ ላይ የሰራውን ግፍና በደል ለመሸፈን ስሙን ዐማራ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ዐዴፓ) ብሎ እ.ኢ.አ መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ/ም ራሱን ሰየመ።

 በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ኢትዮጵያ በዓይን የሚታየው ገሃድ አንድ እና አንድ ነው። እርሱም የኦሕዴድ-ኦዴፓ-ኦነግ (ኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር) ወራሪነትና ተስፋፊነት ብሎም የኦሮሞ የበላይነት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የታገለለት እና ውድ ሕይወቱን የገበረበት የእኩልነት፣ የነጻነት እና የዴሞክራሲ ትግል ለጊዜው በጥገናዊ ለውጥ ማታለያ ስም ረገብ ብሏል ። ይኸው የጊዜ ጉዳይ እንጂ ረገብ ያለውና የተዳፈነው ስርነቀል አብዮት ፍንድቶ ይወጣል። ለምን ቢባል? እኩልነት፣ ነጻነት እና ዴሞክራሲ በሌለበት ቦታ ጭቆና ስላለ፤ ለእኩልነት፣ ለነጻነት እና ለዴሞክራሲ የሚደረግ ትግል ደግሞ ጭቆናን አሽቀጥሮ ለመጣል አመጽን ስለሚወልድ ነው። የህብረተስብ ሳይንስ እና የዓለም ታሪክ የሚያስተምረን ይህኑን ነውና።

4.   ከአራት አሥርታት ዓመታት በኋላ ከእንቅልፉ የባነነው ኢሕዴን-ብአዴን-አዴፓ

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም እ.ኢ.አ. በከፍተኛ ደረጃ በተቀነባበረ ሴራ አራት(4) የዐማራ “ክልል” ከፍተኛ መሪዎች ከተገደሉ በኋላ እና በሽዎች የሚቆጠሩ የዐማራ ተወላጆች በመላው ኢትዮጵያ እየታደኑ በሚታስሩበት ወቅት፤ መላው የዐማራ ሕዝብ በታላቅ ሃዘን ድባብ ውስጥ ባለበት ሁኔታ፤ የኢሕዴን-ብአዴን-አዴፓ ፈጣሪ ትሕነግ/ሕወሓት ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ/ም እ.ኢ.አ. ባወጣው መግለጫ የሰኔ 15ቱ ቀን ግድያ ተጠያቂ ጠፍጥፎ የፈጠረው ልጁና ተላላኪው ኢሕዴን-ብአዴን-አዴፓ ነው ሲል ወንጅሎ፤ ለዚህም ይቅርታ መጠየቅ አለበት በማለት  በዐማራው ላይ ሃዘን እና ንዴት ጨመረበት።

በዚህ ጊዜ ነበር፤ ባለፉት 28 ዓማታት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ቅጽበት ፤ ኢሕዴን-ብአዴን-አዴፓ ከ40 ዓመታት በኋላ ከእንቅልፉ ባንኖና እንደ አንበሳ እያገሳ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ ፈጣሪውን ትሕነግ/ሕወሓት በላፉት 28 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሰራውን ወንጀል እና ግፍ ጆሮን ለማመን እስከ ሚከብድ ድረስ እስከ አፍንጫው ልክ ልኩን በመንገር ድባቅ የመታው። በእውነት ይኸን መግለጫ ያወጣው፤ አዲስ ጌታ ኦሕዴድ-ኦዴፓ-ኦነግ ስለአገኘ የድሮ ጌታውን ከድቶ ነው? ወይስ በእውነት የኢሕዴን-ብአዴን-አዴፓ ከ40 ዓመት እንቅልፉ ባንኖ ተነስቶ ለዐማራው ሕዝብ አልኝታ ሆኖ መውጣቱ እና መቆሙ ይሆን? ጊዜ ሚዛኑ እና ዳኛው  እውነቱን እያሳዬን ነው።

የዚህን ድርጅት ረጅም ታሪክ ለሚያውቅና ለተከታተለ ሁኔታውን ለማመን እጅግ በጣም ይከብዳል። ለምን ቢሉ፤ ወገናችን የዐማራ ሕዝብ ኢሕዴን-ብአዴን-አዴፓን ለረጅም ዓመታት ቢያየው፣ ቢያየው ታጥቦ ጭቃ ስለሆነበት፤ እንዲሁም የትሕነግ/ሕወሓት ተላላኪ በመሆን ዐማራውን ሕዝብ ክፉኛ ስለጎዳው እና ስለአስመታው ነው። ለዚህ በቂ ማስረጃ የሚሆነው፤ ባለፉት ጥቂት ወራት የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ ባደረገው ታላቅ ሰላማዊ ስልፍ ላይ ይዞት ከወጣቸው መፈክሮች አንዱና በሃገር ቤትና በውጪ ሃገራት የሚኖረውን የዐማራ ተወላጅ ዓይን የሳበው መፈክር እንዲህ ይል ነበር፥

 “ አዴፓን አማራ ከማድረግ  ሠይጣንን መልአክ ማድረግ ይቀላል”

ይህ ከፍተኛ ቁጭትና ንዴት ያለበት መልዕክት ነው። ምድር ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በግልጽ የሚያንጸባርቅ ነው ተብሎ በአብዛኛው ዐማራ እንድሚታመን እንገምታለን።

5.    ኢሕዴን-ብአዴን-አዴፓ በእውነት ተለውጫለሁ፣ ዐማራ ሁኛለሁ፤ ለዐማራ ሕዝብ ኅልውና፣ ማንነትና

ልዕልና ቁሜአለሁ ካለ፤ በሚከተሉት ዓበይት ጉዳዮች ላይ በይፋ ግልጽ መልስ እንዲሰጥ እና እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፤

1ኛ/ ትሕነግ/ሕወሓት በዐማራው ሕዝብ ላይ  ባካሄደው የዘር ማጽዳት ( ethnic cleansing)  እና የዘር ጭፍጨፋ (genocide) ግምቱ ወደ 5.5 ሚሊዮን የሚገመት የዐማራ ተወላጆች ማለቃቸውን በይፋ እውቅና መስጠትና ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም ህብረተስብ ማሳወቅ፤

2ኛ/ ይኸን ከፍተኛ የዘር ማጽዳትና ጭፍጨፋ ያክሄዱ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ፤

3ኛ/ የዐማራው ሕዝብ በደረሰበት በዚህ የዘር ማጽዳትና ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል፣ ሃብትና ንብረት ውድመት እና ከፍተኛ የስነ-ልቦና ስብራት ደርሶበታል። ለዚህም፣ ተገቢው ካሳ በሕይወት ላሉ ቤተሰቦቹ፤ ሃብትና ንብረታቸው አጥተው ለተፈናቀሉት የኑሮ መቋቋሚያ እንዲያገኙ ማድረግ፤

4ኛ/ የዐማራው ሕዝብ ስይወከልበት በላዩ ላይ የተጫነበት የአፓርታይድን ሥርዓት፤ በኢትዮጵያ የተመሠረተውና ትሕነግ/ሕወሓትና ኦነግ በጥምር ያዘጋጁት አግላዩ ሕገ-መንግሥት የዐማራው ሕዝብ እንደማይቀበለውና እንደማይወክለው በይፋ መግለጽ፤

5ኛ/ በትሕነግ/ሕወሓትና በኦነግ አከላለል በጉልበት የተውስዱትን የዐማራ ሕዝብ አጽመ-ርስቶች ማለትም፥ መተከል፣ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ራያ፣ አለማጣ ወዘተ... የዐማራው ሕዝብ አጽመ-ርስቶቹ እንደሆኑ በይፋ ማሳወቅ እና የሚመለሱበትን መንገድ ከዐማራው ሕዝብ ጋር ተመካክሮ መሥራት፤

6ኛ/ የዐማራ “ክልል” ከሚባለው ውጭ ለብዙ ሽህ ዓመታት በመሃል፣ በምስራቅ፣ በምዕራብ እና በደቡብ ኢትዮጵያ የሚኖሩት ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን የሚገመተው የዐማራው ሕዝብ አካል እንደሆኑና ኢሕዴን-ብአዴን-አዴፓ እራሳቸውን የማስተዳደር፣ የመኖርና በነጻ የመንቀሳቀስ እንዲሁም በቋንቋቸው መጠቀምና ማስተማር መብታቸው እንዲያስጠብቅ ይኸኑን በይፋ በመግለጽ በተግባር ማሳየት፤

7ኛ/ በሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ/ም እ.ኢ.አ. በባሕር ዳር ከተማ በተቀናበረ መንገድ የተካሄደው ግድያ በገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ/ ኮሚሽን እንዲጣራና ጠቅላላ ውጤቱ በይፋ ለሕዝብ እንዲገለጽ እንዲሆን ማድረግ፤

8ኛ/ በዚሁ በስኔ 15 ቀን ግድያ ሳቢያ ለፖለቲካ ሽፋን ሲባል በተንኮልና በሴራ በክልሉ ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙት ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ ኮሎኔል አማረ አለበል፣ ሌሎች ከፍተኛ መኮንኖች፣ የዐማራ ብሔራዊ  ንቅናቄ (ዐብን) አመራር፣ አባላትንና ደጋፊዎች፣ ባለሃብቶች፣ ወጣቶች፣ ወዘተ... የክልሉ መስተዳድር በአስቸኳይ እንዲፈታቸው፤ ከዚህም በላይ፣ በመላው ኢትዮጵያ የዐማራ ጀግና ልጆችን እንደ አውሬ ማሳደዱና ማደኑ በአስቸኳይ እንዲቆም እንዲያደርግ፤

9ኛ/ በሰኔ 15 ቀን ግድያ ተያይዞ በዐማራ “ክልል” የገባው ወራሪ የፌደራል ሠራዊት በአስቸኳይ የዐማራን ክልል ለቅቆ እንዲወጣ ማድረግ፤

10ኛ/ የዐማራው ሕዝብ ከላይ ከታች የተጋረጠበትን ከፍተኛ የኅልውናና የማንነት አደጋ ለመቋቋም እንዲችል፤ የዐማራውን ሕዝብ በአስቸኳይ ማደራጀትና ማዘጋጀት ይቻል ዘንድ ማገዝ፤

አዲሱን የክርስትና ስም እንጠቀምና - አዴፓ! በትሕነግ/ሕወሓት ላይ ባወጣው ታሪካዊና ጠንካራ መግለጫ የድሮ አለቃውን-ትሕነግ/ሕወሓት የማይድን በሽታ አለበት እንዳለው፤ የዐማራ ሕዝብም አዴፓን የማይለቅ የሎሌነትና የአሽከርነት በሽታ አለበት ይላል። አሁን ግን፣ እንደ አንበሳ እያገሳ ካወጣው መግለጫ አንጻር አዴፓ ዐማራ ይሁን! ዐማራ መሆን በተግባር ያሳይ! አለበለዚያ፣ የኦሕዴድ-አዴፓ-ኦነግ የትሮይ ፈረስ በመሆን የሚጋለበው፣ ለጊዜው ረገብ ያለው ሆኖም ግን የማይቀረው ሕዝባዊ ማዕበል እስክሚመጣ ድረስ ብቻ ነው። ይህ አይቀሬ መሬት አንቀጥቅጥ ሕዝባዊ ማዕበል የመጣ ጊዜ የታሪክ ትቢያ ይሆናልና። ይህ ከመሆኑ በፊት፣ አሁንም በድጋሜ የምንለው አዴፓ ዐማራ ይሁን ነው። የአዴፓ የተግባር እውነታ በዐማራው ላይ ሸክም ሆኖ ለብዙ አመታት ያደረሰው መጠነ ሰፊ ጉዳት መሆኑ ቀርቶ፣ ለዐማራው ሕዝብ ኅልውና እና ማንነት ዘብ ቁሞ አኩሪ ታሪክ የመስራት እንዲሆን በማሳሰብ ነው። 

አንድ ዐማራ ለሁሉም ዐማራ
ሁሉም ዐማራ ለአንድ ዐማራ!
የዐማራው ሕዝብ ኅልውናና ማንነት በጀግና ልጆቹ ይከበራል!

ድል ለዐማራ ሕዝብ!
ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃልኪዳን ነው!