Author Topic: Finote Democracy ፍካሬ ዜና -ታኅሣስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. (30 December 2018 Weekly NEWS SUMM  (Read 3011 times)

staff3

  • Global Moderator
  • Newbie
  • *****
  • Posts: 260
Finote Democracy ፍካሬ ዜና -ታኅሣስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም.
(30 December 2018 Weekly NEWS SUMMARY)
   
EPRP PR   
   
#ርዕሰ ዜና#
#በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በድንበር፣ በግጦሽ መሬት፣ በመማሪያና በሥራ ቋንቋ ምርጫ፣ መሬት ለቃችሁ ውጡ ግጭቱ ቀጥሏል
#አሁንም በሜቴክ ስም በርካታ ገንዘብ እየተዘረፈ መሆኑን ማወቅ ተችሏል
#ኤርትራ ድንበሯን የዘጋችበት ምክንያት እያነጋገረ ነው ተባለ
#የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ስብሰባ መዘጋጀቱ ተሰማ
#በአዲስ አበባ የዳቦ ዋጋ ጭማሪ ሊደረግ መሆኑ እየተሰማ ነው
#ባንኮች ግዙፍ ብድሮችን ለመፈጸም የአቅም ውስንነት ስላላቸው ግንባታዎች እየተስተጓጎሉ መሆኑ ታወቀ
#ከኢትዮጵያ ህዝብ እሩቡ በአእምሮ ህመም እንደሚሰቃይ ተገለጸ

##ዝርዝር ዜናዎች##   

#በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በድንበር፣ በግጦሽ መሬት፣ በመማሪያና በሥራ ቋንቋ ምርጫ፣ መሬት ለቃችሁ ውጡ ግጭቱ ቀጥሏል
 በተለያዩ  የሀገሪቱ  አካባቢዎች  በድንበር፣  በግጦሽ መሬት፣  በመማሪያና  በሥራ ቋንቋ  ምርጫ፣ መሬት  ለቃችሁ ውጡ በሚል ጽንፈኛ አመለካከት ኩታ ገጠም የሆኑ ጎሳዎች እየተጋጩ በርካታ ሰዎች እየተገደሉና በጽኑ እየቆሰሉ መሆናቸውን ከተለያዩ ምንጮች  መረዳት  ተችሏል፡፡  በአንዳንድ  አካባቢዎች  የጤና  ተቋማት  ለቁስለኞች ህክምና  እንዳይሰጡ  ዛቻ ያዘሉ  መልዕክቶች  እየተላለፉ  መሆናቸውም  ይነገራል፡፡ በወለጋ  የሚካሄደው  ግጭት  ምንም  እንኳ  ኦነግ  የማያዘው ያፈነገጠ ኃይል እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት የተገለጸ ቢሆንም፣ ኦነግ ሊታመን እንደማይችል በርካቶች ያስረዳሉ፡፡ ወለጋ ላይ  እየተካሄደ  ያለው  ሕዝባዊ  ቀውስ  በሐረር፣  በባሌና  በአርሲ እንደሚከሰት ስጋት  ማሳደሩን  መገንዘብ  ተችሏል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ጉጂና ቡርጂ፣ አፋርና ኦሮሞዎች፣ አፋርና ኢሳዎች፣ ተጋጭተው በርካታ ንፁሀን ዜጎች ተገድለዋል፡፡ ይህን መሰል ግጭቶች ሊስፋፉና በየቦታው የእርስ በእርስ ግጭቶች ሰዎች ሊፈናቀሉ፣ ሊገደሉ፣ ንብረቶቻቸው ሊዘረፉ፣ እናቶችና እህቶች ሊደፈሩ ይችላል የሚል ስጋት ያሳድራል ተብሎ እየተሰጋ ነው።

#አሁንም በሜቴክ ስም በርካታ ገንዘብ እየተዘረፈ መሆኑን ማወቅ ተችሏል
 ሜቴክ የሚለውን ስያሜ አዲስ የሚባለው ዘረኛ አገዛዝ በመቀየር ኢኮሥኮ ማለቱ የሚታወስ ሲሆን አዲሱ ሜቴክን አዲሱ  አገዛዝ  እያሠራው  መሆኑ  ሲታሰብ  አዲስ የሙስና  መረብ  እየተዘረጋ  ነው  የሚል  ጥርጣሬ  እያጫረ  ነው ተብሏል፡፡  በቅርቡ አራት  ኪሎ  የሚገኘው  የጠቅላይ ሚንስት ገንዘብ  በኢኮሥኮ  እየተገነባ  እንደሆነ መረዳት  ተችሏል፡፡  ይህ  አጥር  በኮሎኔል  መንግሥቱ  ዘመን  ከአምስት  ጊዜ በላይ እየፈረሰ  መገንባቱ  የሚታወስ  ሲሆን  በመለስም  ከሁለት  ጊዜ  በላይ  መሰራቱ የሚታወስ  ነው  ተብሏል፡፡ በአሁኑ የጨረባ ፖለቲካም ወቅትም ከሁሉ አስቀድሞ ይህ አጥር አፍርሶ አጥር መገንባት ወቅታዊነቱ ሌላ ሳይሆን ገንዘብ ለመቀርጠፍ በስሌት የተገባበት መሆኑ እንደማያጠራጥር ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡ መድኃኒት መግዣ በጠፋበት፣ ነዳጅ  በዱቤ  በሚመጣበት፣  ውሀና  ኤሌክትሪክ  በወረፋ  በየአስራ  አምስት  ቀኑ በሆኑበት፣  ጎዳና  የሚኖሩ  ህፃናት እየበዙ ባለበት፣ የአጥር ግንባታው አነጋጋሪነት እየጨመረ መሆኑን ተረድተናል።

#ኤርትራ ድንበሯን የዘጋችበት ምክንያት እያነጋገረ ነው ተባለ
 በአፍሪካ ረጅም ዘመናትን ካስቆጠሩ አምባገነን ገዢዎች አንዱ የሆነው ኢሳያስና የቢጤው ዘረኛ አገዛዝ መሞዳሞድ የአገዛዞቹ  እንጂ  የሕዝብ  ባለመሆኑ  ሳይውል ሳያድር  መፈረካከሱ  የማይቀር  መሆኑ  እየተነገረ  ነበር፡፡ ከታማኝ ምንጮች  ከተገኘው መረጃ፣  ታህሳስ  አምስት  ኢሳያስ ወደ  ሶማሊያ  ባቀናበት ወቅት  አምባገነኑን  ቡድን ከሥልጣን ለማስወገድ  ማሴራቸው የተደረሰባቸው በርካታ የጦር መኮንኖች ኢራ  ኢሮ በሚባል  እስር  ቤት  መታሰራቸው ታውቋል፡፡ በዚህ የከፍተኛ መኮንኖች እስር ስብሀት ኤፍሬም ተጠያቂ በመሆኑ እሱን ለማስወገድ የመጀመሪያው ዙር የሳዋ  ሰልጣኝ  የነበረና ከኤርትራ  ጠፍቶ  ኢትዮጵያ  ውስጥ  የሚኖር  የተጀመረውን  ነፃ  ዝውውር በመጠቀም ወደ ኤርትራ የገባ ሲሆን የበቀል እርምጃ በስብሀት ኤፍሬም ላይ እዲወስድ ይህን መፈንቅለ­መንግሥት ካቀነባበረው ቡድን መመሪያ ተሰጥቶት ያደረገው መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡ የታሰሩት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በአሁኑ ወቅት በኢሳያስ ቀጥተኛ ቁጥጥር ስር ወደሚገኘው ማርያም ግቢ ወህኒ ቤት ተዛውረው ቁም ስቅላቸውን እያዩ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ ሱዳን እየጋመ ያለው የለውጥ ቋያ ኤርትራ ውስጥም መቀጣጠሉ አይቀርም እየተባለ ነው፡፡ ከእንግዲህ ኢሳያስ እያሰረና እየገደለ የኤርትራ ሕዝብን እየረገጠ የመግዛት የመጨረሻው  ምዕራፉ  ሊዘጋ መቃረቡን  በርካቶች ያስረዳሉ።

#የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ስብሰባ መዘጋጀቱ ተሰማ
 ባሳለፍነው  ሳምንት  ከተለያዩ  የሁለተኛ  ደረጃ  ትምህርት  ቤቶች  ከተገኘው መረጃ  ዘረኛው  አገዛዝ  የመምህራን ተወካዮችን ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን ነው፡፡ የስብሰባው አስፈላጊነት ከትምህርት ሥራ ጋር ቀጥኛ ተዛምዶ ባለው ርእስ  ላይ  ሳይሆን  ዋነኛው ጉዳይ  እየተስፋፋ  ያለውን  የጎሳ  ግጭት  ለማስቆም  መምህራንን  “በሰላም  ካድሬነት” ለመጠቀም ታስቦ ነው ተብሏል፡፡ በስብሰባው መምህራን የደሞዝ ጭማሪን፣ የትምህርት ጥራትን፣ በትምህርት ቤቶች የተሰንራፋውን የሙስና ወረርሽኝን፣ ከሁሉም በላይ ህጋዊ ማህበራቸው የተገፈፈው የመንቀሳቀስ መብቱ እንዲከበርና አሁን በመምህራን  ስም የማህበሩ መሪ ነን የሚሉት በወያኔ የተሰየሙ በመሆናቸው እንዲሰናበቱ አንስተው መሟገታቸው አይቀርም ተብሏል።

#በአዲስ አበባ የዳቦ ዋጋ ጭማሪ ሊደረግ መሆኑ እየተሰማ ነው
 በርካታ  የዳቦ  መጋገሪያዎች  በህገ­ወጥነት  የዳቦ  ዋጋ  ጨምረዋል፣  የዳቦውንም መጠን  ቀንሰዋል፡፡ በተጨማሪም ብዙዎቹ ዳቦ መጋገሪያዎች የዳቦ አመራረታቸውና የሚያመርቱበት  ሁኔታና  ቦታ  ለጤና  በጣም  ጠንቅ  ናቸው ተብሏል፡፡ ይህን  ሁኔታ ለማስተካከል  ምንም  ዓይነት  እርምጃ  ሳይወሰድ  ባለበት  የዋጋ  ጭማሪ  ለማድረግ በሕግ እንዲፈቀድ ከዳቦ ጋጋሪዎች የቀረበው ጥያቄ እያነጋገረ ነው ተብሏል፡፡ ይህ የዳቦ ዋጋ ጭማሪ በእርግጥም ከአጠቃላይ ገበያው  ጋር  በተያያዥነት  መቅረቡ ሲታወቅ ዋናው  ጉዳይ  ግን  ከአብዛኛው  ሕዝብ  አቅም  ጋር  ሊገናዘብ  ይገባዋል የሚል አስተያየት ሲሰጥ ይሰማል፡፡ ጭማሪው ከነዳጅ ዋጋ፣ ከውጪ ምንዛሪ፣ ከቤት ኪራይ፣ ከሠራተኛ ደሞዝ ጋር በተያያዘ የቀረበ ሲሆን በሌላ አንፃር ደግሞ የሕዝቡ የመግዛት አቅም ደካማ በመሆኑ ይህ ዳቦ ላይ የሚደረግ ጭማሪ በሱዳንና በቱኒዚያ የተከሰቱ አመጾችን ሊያስከትል ይችላል የሚል ግምት እየተሰጠ ነው ተብሏል።

#ባንኮች ግዙፍ ብድሮችን ለመፈጸም የአቅም ውስንነት ስላላቸው ግንባታዎች እየተስተጓጎሉ መሆኑ ታወቀ
 እንደሚታወቀው  ለግዙፍ  የግንባታ  ሥራዎች  የግል  ባንኮች  አቅማቸው  ደካማ በመሆኑ  በማበደሩ  ተሰማርተው አያውቁም፡፡ ለግዙፍ የሆቴል ግንባታዎች ብድር የሚያቀርቡት ሁለቱ የመንግሥት ባንኮች ንግድ ባንክና ልማት ባንክ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሁለቱም ባንኮች አቅማቸው በመመናመኑ ምክንያት ሠላሳ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ገንባታቸው መስተጓጎሉ ታውቋል፡፡ አንዳንዶቹ ሆቴሎች የማጠናቀቂያ ማለትም  ቁሳቁሶችን  ከውጪ  ማስመጫ ገንዘብ  የሚያስፈልጋቸው  መሆኑን  አቅርበው  ገንዘብ ባለመኖሩ የጠየቁትን ብድር ባለማግኘታቸው ጊዜ  እየነጎደ አላግባብ ለተጨማሪ ክፍያ እየተዳረጉ መሆናቸውን በምሬት ያስረዳሉ

#ከኢትዮጵያ ህዝብ እሩቡ በአእምሮ ህመም እንደሚሰቃይ ተገለጸ
 በቅርቡ ይፋ ከተደረገ አንድ በአእምሮ ህሙማን ላይ ከተደረገ ጥናት መገንዘብ የተቻለው በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር  እየጨመረ  በመሄድ ላይ መሆኑን  ነው፡፡ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ  አራተኛ  የሚሆነው በተለያዩ የአእምሮ  ህመሞች እንደሚጠቃ  በጥናቱ  የተጠቆመው  አስደንጋጭ ነው ተብሏል፡፡  የበሽታው መስፋፋት መንስኤ ሆነው የቀረቡት የአልኮና የአደንዛዥ እጾች ሱሰኝነት፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው  የቤተሰብ  መዋቅር  መፈራረስ፣ የሥራ  ዋስትና  አለመኖር፣ የአእምሮ  ሀኪሞችና የስነልቦና  ባለሙያዎች  እጥረት፣  ከሁሉም  በላይ  ደግሞ  የሰላማዊ ሁኔታ መጥፋት እንደሆኑ መረዳት ተችሏል።

#ለዝርዝር ዜናዎች > ከታች ይጫኑ (to listen detail news click below)
To Read: http://www.finote.org/Fikarezena.pdf
To Listen PART 1: http://www.finote.org/Today_Part1.mp3
You Tube: https://youtu.be/3cpghLpfk_U