Author Topic: Finote Democracy ፍካሬ ዜና -ኅዳር 23 ቀን 2011 ዓ.ም. (02 December 2018 Weekly NEWS SUMMA  (Read 2914 times)

staff3

  • Global Moderator
  • Newbie
  • *****
  • Posts: 260
#Finote Democracy ፍካሬ ዜና -ኅዳር 23 ቀን 2011 ዓ.ም. (02 December 2018 Weekly NEWS SUMMARY)

#ርዕሰ ዜና #በወለጋ ቀውሱ እንደቀጠለ መሆኑ ተነገረ
#ጭንሀክሰን ሰቆቃዋ መደገሙ ተሰማ
#የሕገ­ወጥ የመሣሪያ ዝውውር አሳሳቢነቱ እየጨመረ መሆኑ ታወቀ #የአገዛዙ የንግድ ድርጅቶች በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባቸው እየተነገረ ነው #የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መሄዱን አንድ በጉዳዩ ላይ የተካሄደ ጥናት ጠቆመ

##ዝርዝር ዜናዎች##

#በወለጋ ቀውሱ እንደቀጠለ መሆኑ ተነገረ
 ከመንፈቅ  በላይ  እያስቆጠረ  ያለው  የምዕራብ  ወለጋና  የቤንሻንጉል  ጉሙዝ  አካባቢ  የጸጥታ  ሁኔታ  ከጌዜ  ወደ  ጊዜ እየተባበሰ መሄዱ  አካባቢውን ወደ  አልተጠበቀ ምስቅልቅል ቀውስ ሊያስገባ ይችላል  የሚል  ስጋት ማሳደሩ እየተነገረ
ነው  ተባለ፡፡  የቤንሻንጉል  ታጣቂ  ኃይል  መሆናቸው  የሚነገርላቸው  በቀስትና  በዘመናዊ  መሣሪያ  በአካባቢው  እየኖሩ የሚገኙትን ኦሮሚኛ ተናጋሪዎችን እና ሌሎችን ይውጡልን በሚል ቤቶች እያቃጠሉ፤ ንብረት እየዘረፉና ከብት እየነዱ፤ ሴቶችን እየደፈሩ፤ የሚሸሸውን ሕዝብ ከጀርባ ተኩስ በመክፈት በርካቶችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል ከመቶ ሺ በላይ ሕዝብ  መፈናቀሉ  እየተነገረ  ነው፡፡  ይህ  የሕዝብ  መፈናቀል  ለስድስት  ወራት  ያለማቋረጥ  መቀጠሉ  ዘረኛው  አገዛዝ በንፁሀን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ ለመታደግ ምንም ዐይነት እርምጃ አለመውሰዱ በአካባቢው የሚካሄደው ግጭት ወደ  የለየለት  የእርስ  በእርስ  ግጭት  እየሆነ  እንደሆነ  ሁኔታውን  የሚከታተሉ  የፖለቲካ  አዋቂዎች  ያስረዳሉ፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ከአስር የሚበልጡ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላት መገደላቸውን ተከትሎ በአምቦ፣ በነቀምት፣ …ወዘተ የተቃውሞ  ሰልፎች  መካሄዳቸው  ተሰምቷል፡፡  ለጉዳዩ  ትኩረት  እንደተሰጠው  ለማስመሰል  ኦዴፓ  ስብሳባ  ተቀምጦ ውሳኔ ማስተላለፉ ብዙዎችን  እያነጋገረ መሆኑ ታውቋል፡፡  እንዲህ ያለው  ሀገራዊ ጉዳይ  እንጂ  የአንድን አካባቢ ብቻ የሚመለከት  ባለመሆኑ ሊወሰድ  የሚገባው  እርምጃ  በሀገር  ደረጃ ሊሆን ይገባው  ነበር ተብሏል፡፡  በነቀምት  በተለያዩ መጠለያዎች  ተጠልለው  የሚገኙ  ተፈናቃዮች  እስካሁን  ተገቢ  የሆነ  ትኩረት  ባለማግኘታቸው  በቂ  እርዳታ፣  የህፃናት ምግብ፣ መድሀኒቶች፣ አልባሳት፣ …ወዘተ ባለማግኘታቸው ስቃያቸውን እያባባሰው መሆኑን ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ  በዚህ  ከቀጠለ፣  ከዚህ  ቀደም  ከምሥራቅና  ከምዕራብ  ሐረርጌ  የተፈናቀሉ  ለዓመታት  ወደ  ቀያቸው  ሳይመለሱ ተበታትነው እንደቀሩት ወገኞች ያለ ክስተት መከሰቱ አይቀሬ መሆኑን በርካቶች ያስረዳሉ።

#ጭንሀክሰን ሰቆቃዋ መደገሙ ተሰማ
 በጭንሀክሰን  ባሳለፍነው  ሳምንት  በኗሪዎቹ  ላይ  በተከሰተ  ድንገተኛ  ወረራና  ጥቃት  ከአስራ  አንድ  ሰዎች  በላይ መገደላቸውን መረዳት ተችሏል፡፡ የአካባቢው ሰላም መደፍረስ አሁን በእስር የሚገኘው አብዲ ኢሌ የሚያዛቸው ጀሌዎች የሚፈጽሙት  እንደነበርና  ሁኔታ  ሰውየው  ከታሰረ  ወዲህ  የሶማሌ  ልዩ  ኃይል  የተባለው ሙሉ  በሙሉ ትጥቁን  እንደፈታና  መዋቅሩ  መፈራረሱ  መነገሩ  የሚታወስ  ነው  ተብሏል፡፡  የሰሞኑን  ጥቃት  የፈጸመው  ኃይል ማንነቱ  ያልታወቀ  ተብሎ  መገለጹ  በርካቶች  ሁኔታውን  በጥሞና  መመልከት  እንደሚያስፈልግ  ያስረዳሉ፡፡  ይህ ማንነቱ  ያልታወቀ  የተባለው  ኃይልን  ከሶማሌው  ሽብርተኛ  ቡድን  አልሸባብ  ጋር  የሚያያይዙት  ጥቂቶች አለመሆናቸውን መገንዘብ ተችሏል።

#የሕገ­ወጥ የመሣሪያ ዝውውር አሳሳቢነቱ እየጨመረ መሆኑ ታወቀ
 በኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ በትንሹ ባለፉት ስድስት ወራት የጦር መሳሪያ ዝውውር ታይቶ በማታወቅ ሁኔታ በገፍ  ከጠረፍ  ወደ  መሀል  ሀገር፣  ከመሀል  ሀገር  ወደ  ተለያዩ  አቅጣጫዎች  እየተሰራጨ  መሆኑን  በተለያዩ  ጊዜያት ከፖሊስ  ከተሰጡ መግለጫዎች መገንዘብ  ተችሏል፡፡  የመሣሪያዎቹ  ዐይነቶች  በብዛት  ቱርክ ሠራሽ  ሽጉጦች፣ የእጅ ቦምቦች  እና  ክላሽን  ኮቮች  መሆናቸው  ጉዳዩን  አሳሳቢ  ያደርገዋል  ተብሏል፡፡  ሰሞኑን  ከታማኝ  ምንጭ  የተገኘው መረጃ አዲስ አበባ ውስጥ ተቀጣጣይ ቦምቦች መያዛቸው የመሣሪያ ዝውውሩ ጦስ ማስከተሉ አይቀርም የሚል ስጋት ማሳደሩ እያነጋገረ ነው ተብሏል።

#የአገዛዙ የንግድ ድርጅቶች በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባቸው እየተነገረ ነው
 የዘረኛው አገዛዝ የፖለቲካ ድርጅቶች በሕዝብ ስም እና የፖለቲካ ድርጅቶቻቸውን የገንዘብ አቅም ለማጠናከር በሚል ብአዴን  በጥረት፣  ህወሓት  በኤፈርት፣  ኦህዴድ  በዲንሾ፣  …ወዘተ  ስም  የሚንቀሳቀሱት  የንግድ  ድርጅቶችን  በሕግ አግባብ  አደብ ማስያዝ  የግድ  ነው ተብሏል፡፡  እነዚህ  የንግድ ድርጅቶች  እራሱ  አገዛዙ  የደነገገውን ሕግ ተላልፈው የተቋቋሙና ለድርጅቶቹ የበላዮች ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ መሆናቸው በስፋት ይነገራል፡፡  በሌላ አንፃርም እነዚህ የአገዛዙ  የፖለቲካ  ድርጅቶች  የንግድ  ተቋማት  የንግዱን  እንቅስቃሴ  እድገት  በከፋ  ሁኔታ  እየተጸናወቱት በመሆናቸውና  ለበርካታ  የሀገር  ገንዘብ  ዘረፋና  በውጪ  ሀገራት  መከማቸት  እንደ  ዋነኛ  መተላፊያነት  እያገለገሉ መሆናቸውን በርካቶች ሲገልጹ ይሰማል፡፡ በርካታ የፖለቲካ አዋቂዎች እነዚህ የንግድ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ሀብት የተቋቋሙ በመሆናቸውና የጥቂት ፈላጭ ቆራጮች የሀብት ምንጭ በመሆናቸው ድርጅቶቹ ሊከበሩና ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ሊደረግ ይገባል ተብሏል።

#የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መሄዱን አንድ በጉዳዩ ላይ የተካሄደ ጥናት ጠቆመ
 በድፍን  ሀገሪቱ  ወጣቶች  ከተለያዩ  የትምህርት  ተቋማት  ተመርቀው  ከወጡ  በኋላ  ሥራ  ማግኘት  ፍዳ  መሆኑን በምሬት ሲያስረዱ  ይሰማል፡፡  በተለያዩ  የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች  ለመቀጠር  አንዱ  ከዘረኛው  አገዛዝ  የፖለቲካ
ድርጅቶች ውስጥ የአንዱ አባል መሆን ከመመዘኛዎቹ ውስጥ ዋነኛው መሆኑ ይነገራል፡፡ በሁለተኛነት የሚጠቀሰው ሥራ  ለማግኘት  ዝምድና፣  አምቻ፣  መንደርተኝነት፣  ጉቦ  መክፈል፣  …ወዘተ  የሚጠቀሱ  ሲሆኑ  እነዚህም  ብዙዎቹን ለሥራ አጥነት እየዳረጉ ያሉ መሆናቸውን በሥራ ፍለጋ የደከሙ ወጣቶች ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የህንፃ ግንባታዎች በተለያዩ ሰበቦች በመቋረጣቸውና በመቆማቸው የተለያዩ የህንፃ ግንባታ ባለሙያዎች ከሥራ እየተቀነሱና ለችግር በመጋለጣቸው የሥራ አጥ ወጣቶችን ቁጥር በመጨመሩ በኩል የራሱ ተጽእኖ እንዳለው ከአንድ በጉዳዩ ላይ ከተካሄደ ጥናት መገንዘብ መቻሉን ብዙዎች ያስረዳሉ።

#ለዝርዝር ዜናዎች > ከታች ይጫኑ (to listen detail news click below)

To Read: http://www.finote.org/Fikarezena.pdf
To Listen PART 1: http://www.finote.org/Today_Part1.mp3
You Tube: https://youtu.be/CBTKR908OVQ
« Last Edit: December 02, 2018, 04:13:58 PM by staff3 »