Author Topic: ኢሕአፓ አንድና አንድ ብቻ ነው  (Read 4767 times)

staff3

  • Global Moderator
  • Newbie
  • *****
  • Posts: 260
ኢሕአፓ አንድና አንድ ብቻ ነው
« on: September 21, 2018, 12:30:50 PM »
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ( ኢሕአፓ )
Ethiopian People´s Revolutionary Party (EPRP)

መስከረም 10 ቀን 2010 ዓ.ም.

ይድረስ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ

ኢሕአፓ አንድና አንድ ብቻ ነው

(PDF Version)
http://eprp.com/press_releases/EPRP_Pressrelease_Sept202018.pdf

መስከረም 12 ቀን አዲሶቹ ባለስልጣኖች ኢሕአፓ ነን የሚሉ ሕገ ወጥ ግለሰቦችን ወደ አዲስ አበባ ጋብዘው አቀባበል ሊያደርጉላቸውና በድርጅቱ ስምም ሊያንቀሳቅሷቸው ያቀዱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል ። እነዚህ ግለሰቦች ኢሕአፓን ከድተው ከሄዱ 10 ዓመታትን አስቆጥረዋል። ባሁኑ ጊዜ እነዚህን ግለሰቦች ጠርቶ መስተንግዶ መስጠት እነ መለስ ዜናዊ ሥልጣን ሲይዙ እንደተደረገው ሁሉ አስመሳዮችን በኢሕአፓ ስም ለማንቀሳአቀስ የሚደረግ ከንቱ ጥረት መሆኑ ሕዝብ ሁሉ አውቆ ይህን ተንኮልና ሴራ ውድቅ እንዲያደርገው እንጠይቃለን ። ኢሕአፓን ማግለልና ማጥፋት የሻእቢያ፤ የወያኔ፤ የግንጠላ ኃይሎችና የፀረ ኢትዮጵያ ባዕዳን ተልዕኮ ሆኖ ለረጅም ዓመታት መቆየቱን የማያውቅ የለም ማለትም እንፈልጋለን ።

በ45 አመታት የኢሕአፓ የትግል ዕድሜ አንጃ የምንላቸው ቡድኖች ተከስተውብናል። ሁሉንም በአቅዋማቸው ልናስተናግዳቸው ሙሉ ጥረት ብናደርግም፤ አቅዋማቸውን ብዙኅኑ የፓርቲው አባል አልቀበል ሲላቸው ከድርጅቱ ሕግና ደንብ ውጪ ሆነውና የብዙሃኑን ውሳኔ ረግጠው አንጃ በመሆን አልፎም ለጠላት በማደር ብዙ ጉዳት ንዳደርሱ በታሪክ ደረጃ ያቀረብነው ነው ። አንጃ የተባሉት የተለየ ሀሳብ በማቅረባቸው ሳይሆን አቅዋማቸው የብዙኅኑን ተቀባይነት ሲያጣ አፈንግጠው በቡድን በመሰለፋቸው ነው ። በመስከረም 12 ቀን ወደ አዲስ አበባ ለመግባት በዝግጅት ላይ ያሉት ግለሰቦች ከአስር ዓመት በፊት “ከመለስ ዜናዊ አገዛዝ ጋር አብረን እንስራ፤ ሕገ አራዊቱን እንቀበል፤ ትግሉን አቁመን እጅ እንስጥ” በማለት ሀሳብ ያቀረቡና አቋዋማቸው ለድርጅቱ አባላት ሁሉ ቀርቦ ተቀባይነትን ሲያጣ የድርጅቱን ጉባኤ ረግጠው የወጡ ናቸው። ከድርጅቱ ከተለዩ በኋላ ከዚያ በፊት ባልታየ መንገድ ራሳቸውን ኢሕአፓ ዴምክራሲ በኋላም ኢሕአፓ አንድነት በሚል ሰይመው የኢሕአፓን ስም ለመቀማት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ በቁጥር ተመናምነው ሲባዝኑ ኖረዋል። ከዚያም ወዲህ ጉባኤ ረግጣችሁ መፈርጠጣችሁና የድርጅቱን ህጋዊ ስም መጠቀማችሁ ስህትተት መሆኑን አምናችሁ ወደ ድርጅቱ ተመለሱና በህጉ መሠረት አቅዋም የምትሉትን ማቅረብ ትችላላችሁ የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም አሻፈረኝ ብለውና ኢሕአፓነትን ተቃርነው ቆይተዋል ።መስከረም 12 ኢሕአፓ ተብለው ለአዲስ አበባ የማወናበድ ተልዕኮ የታጩት እነዚህ ግለሰቦች አንዳንዶቹም መቸም ቢሆን መቸ የድርጅቱ አባል ያልነበሩ፤ አንዳንዶቹም በስነሥርዓት ጉድለት ከድርጅቱ ከዓመታት በፊት የተባረሩ ነበሩ።

ኢሕአፓ አንድና አንድ ብቻ ነው ። ስሙም አርማውም በሕግ የተመዘገበ ነውና አጭበርባሪዎቹን ማስተናገድ ሕገወጥ መሆኑን ለዘመኑ ባልሥልጣኖችም ተነግሯቸዋል ። የጥላቻና የግንጠላ አባውራዎችን እየሰበሰቡ ያሉት ባለስልጣኖችና ባዕዳንም ለኢትዮጵያ የቆመውን ሀገር ወዳድ ድርጅት ስለሚጠሉ አስመሳዮችን ተክተው ሊያጠፉት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው ። ይህ ዘመቻ ሻዕቢያና አረቦችም የሚደግፉት ነው ። ኢሕአፓ ወያኔ ኢሕአዴግ ተጠግኖ መቀጠል ሳይሆን መወገድ አለበት፤ የሽግግር ሂደት ተጀምሮ ወደ ሽግግር መንግስት አምርቶ ሀገራችን ዴሞክራሲና ሕዝባዊ ጉዞ ማድረግ አለባት፤ ሉዓላዊነቷም መረጋገጥ አለበት፤ አንዱን ዘረኝነት በሌላ መተካት የለብንም፤ ሀገራችን የጥላቻ አውሬዎች መፈንጫ መሆን የለባትም በማለቱ ድርጅቱን ለማግለልና በስሙ አስመሳዮችን ለማሰማራት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። የዛሬ 27 ዓመት ፎረም 84 ወዘተ ብሎ ወያኔ የሞከረውን እንዳከሸፍነው ሁሉ አባላት፤ ደጋፊዎችና ሌላውም የኅብረተሰብ ክፍል ይህን ሴራ ሊያከሽፈው ይገባል። በጥቂት ወራት ውስጥ የታየው ሁኔታ ሕጻናትን ጨምሮ ንጹሃንን የሚያርዱ አውሬዎች የሚሰማሩበትና የሀገር ክቡር ሰንደቅ ዓላም ይዘው ተቃውሞ የሚያሰሙ ኢትዮጵያውያን ዱርዬዎች የሚባሉበት ክስተት ነው። ሀገራችን ለከፍተኛና አስከፊ አደጋ ተጋልጣለች፤ኢትዮጵያዊነት እየተጠቃ ነው። ኢትዮጵያን ከጥፋት ለማዳን ከፍተኛ ርብርብ በሚያስፈልግበት በአሁኑ ሰዓት ኢሕአፓ እያካሄደ ያለውን ትግል ለማኮላሸት ስሙን ነጥቀው በቦሌ ወደ አገር የሚገቡት ግለሰቦች የትግሉ እንቅፋት መሆናቸውን ሁሉም ዜጋ እንዲገነዘበው እንፈልጋለን።

ኢሕአፓ አንድና አንድ ብቻ ሲሆን ለወያኔ ኢሕአዴግ አይሰግድም!
ኢትዮጵያዊነት ያቸንፋል !!


EPRP EPRP
P.O.BOX 73337 BP 30022
Washington, DC. 20056 92276 Bois Colombes Cedex
USA France
Tel. 202 291 4217 Fax: 202 291 7645

Website WWW.EPRP.com Email ESPIC@aol.com
« Last Edit: September 21, 2018, 12:40:31 PM by staff3 »