“ኢሕአፓ ናፈቀችን” ሎሬቱና ደብተራው

ቦ አራዳ አባ ሻውል

ግንቦት 1 ቀን 2006 ዓም

ፀጋዬ ገብረ መድኅን፤ ፀገየ ገብረ መድኅን እንደዚሁም ፀጋዬ ገመድኅን አርአያ የተባሉ ግለሰቦች በኤትዮጵያ የታወቁ ባለኪነት ምሁራን ነበሩ/ናቸው፡፡

በግዕዝ የተጻፈ ለሚያነብ ሰው ሆነ የኪነት ሥራዎች የሚወድ ሰው የነዚህ ግለሰቦች ዝና አያውቅም ለማለት አያስደፍርም፡፡ በግዕዝኛ ማኻይም የሆነ ሰው ግን ላያውቃቸው ይችላል ብየ አስባለሁ፡፡

ለመሆኑ እነሱ እነማን ነበሩ ካሉ ደግሞ የት አሉ?
የመጀመሪያው ሰው ሎሬት ተብሎ በጣም በርከት ያሉ ቲያትሮችና ድራማዎች፤ እንደዚሁም ግጥሞች በመጻፍ የታወቀ ባለኪነት ነበር፡፡ ነበር ያልኩት አሁን በሕይወት ስለሌለ ነው፡፡ በኒው ዮርክ ከተማ አርፈዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተጠቀሰው ፀገየ ደግሞ በወያኔ ጉድጋድ እስር ቤት ውስጥ እየማቀቀ የሚገኝ ሲሆን ሦስተኛው ፀጋየ ግና በእነሱ የብዕር ስም እየተጠቀመ በአሜሪካ የሚኖር ጋዜጠኛ ነው፡፡ ለዚህ ርዕስ ያበቃኝም ይከው ጋዜጠኛ መሆኑ ነው፡፡ ኢሕአፓ ናፈቀችኝ በማለት በኢትዮ ሚዲያ የመስዋዕትነት ወንጌል በሚል መጣጥፍ መጻፉ የሚደነቅ ነው። በመጠኑም ቢሆን የግሉን ዕምነትና ታሪክ ነግሮናልና ነው። አጥፍቶ መጥፋት የሚለው መጽሐፉንም መሰረት በማድረግ ይሁን ወደ ደረሰበት ድምዳሜ “ኢሕአፓ ናፈቀችኝ” ለማለት ያስደፈረው? ምን ይሆን ብየ ራሴንና ጛደኞቸን ጠየቅሁ። ብዙዎቹ የደርግ አባል ነበር አሁንም ነው አሉኝ። በበኩሌ ግና አይመስለኝም። በሙያው የሚሠራ ሰው ሆኖ ነገር ግና በሁለት አስተሳሰብ እየተጎተተ ሰዎችን ላለማስቀየም ብሎ የመኻል ሠፋሪነትን የሚያቀነቅን መስሎ ሊታይ ቻለ። በእኔ ዕይታ ግና ይህ ጋዜጤኛ እንደሌሎች የኤትዮጵያ ጋዜጠኞች ያዩትንና የሰሙትን ላይ ላዩን በመተንተን የተካነ ሳይሆን በሚገባ ነገሮችን ይዞታቸውንና ሂደታቸውን የሚያውቅ ሰው ይመስለኛል እያልኩ ነው። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም የፀጋዬዎችን አርአያ ለመከተል የፈለገው። በሥማቸው ለማምታታት ሳይሆን በአስተሳሰባቸው አካሄድ ተማርኮ ይመስለኛል። አሁን ነፃነቱን ስለአወጀ ዕውነቱን ይነግረናል ብዬ አምናለሁ።

እንግዲህ ወደ ዋናው የርዕሱ ጉዳይ ልግባና ሁለቱ ፀጋየ ገብረ መድኅኖች (ፀገመ) እነማን ናቸው? እነማን ነበሩ? ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው። ፀገመ ሊታወቁ የሚገባቸው ሰዎች ናቸውን? ሙያ አላቸው? ሙያውስ ሕዝብንና አገርን የሚጠቅም ነው ወይንም የሚጎዳ? ብዙ አዕምሮን የሚያናውጥ ጥያቄዎች በአንባቢው የሚጉላሉ እንዳሉ በጣም እርግጠኛ ነኝ።

የፀጋዮች ማንነትና ተክለ-ሰውነት፤ ሥራቸውንና ሞያቸው እንደዚሁም ዓላማቸው (የማወቀውን ያህል) በተከታታይ ለመጻፍ እፈልጋሉ። በበለጠ ደግሞ ሌሎች እንደነ ሙሉጌታ ሉሌ ያሉ በቅርብ የነፀጋዮች ሥራቸውም ሆነ እምነታቸው ቢጽፉ ይመረጣል።

ከሁሉ በፊት የእነ ፀጋዮች ዋና መለያቸው አንዱ ሎሬት ሌላኛው ደብተራው ተብለው እንደታወቁ እንስማማ። ለክርክሩ ያመቻል በሚል እንጂ የዕውነት እነዚህ ሰዎች ማዕርጋቸውና ሥራቸው እንዲህ አልነበረም ብለው የሚከራከሩ አይጠፉምና ነው። ሎሬትና ደብተራ የሚባሉ ቃላቶች አንዱ አገር በቀል ሌላው ከውጭ የተወሰደ በመሆኑ ለውይይታችን በጣም ጠቃሚ ናቸው ብዬ አምናለሁ።በኢትዮጵያ አብዮት ፍንዳታና ሂደት የነበራቸው ሚና ለመግለጽ እንጂ አንደኛው ሎሬት ሌላኛው ደብተራ ስለመሆናቸው አይደለም ቁም ነገሩ፡፡

የፀጋዮዎች ክርክርና ፍልስፍና በአብዮታዊ ለውጥ ሳይሆን በአሠራርና በአካሄድ ላይ ነበር አሁንም ነው፡፡ እሱም ኢትዮጵያ (በእኔ አጠራር ኤትዮጵያ) የምትባለው አገር እንዴት ነው የምትራመደው ብትራመድ ደግሞ የራሳውን ሥልሣኔ በማሳደግ ሲሆን አካሄዱ ግና በምን ዘዴና አሠራር ይሆናል? የሚያስፈልገው ለውጥ ከሎሎች አገሮች አካሄድ በመኮረጅ ወይንስ የራሳን ልጆች ፈጠራ ማራመድ በሚሉ ሁለት ፅንሰ-ሐሳቦች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

እንግዲህ የኢትዮጵያ አብዮትና ፀረ አብዮት በነዚህ ሁለት መስመር ያተኮረ ስለነበረ ውስጠ ሚሥጢሩን በሚገባ በመመርመርና በመወያየት ፈንታ በሆነ ባለሆነ ንትርክ እስከ አሁን ድረስ በመተራመስ ላይ እንገኛለን፡፡

ለመሆኑ የሎረቱና የደብተራው ልዩነትና አንድነት ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ የብዙዎች ርዕስ ጉዳይ መሆን አለበት ብዬ ስለማምን እነሆ በጥቂቱ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡

ድህነትና ነፃነት
እነዚህ ቃላቶች መንትዮች ናቸው አብረው የሚጋዙ፡፡አንዱ ከአንዱ ቢለያዩ ችግር ይፈጠራል። ሁለቱን አጣምሮ መጋዝ የኤትዮጵያውያን ባሕሪ ሆኖ ነበር፡፡በሌላ አነጋገር ልብና አዕምሮ በኤትዮጵያውያን ሥነ ልቦና አይለያዩም አብረው ናቸው፡፡ አይነጣጠሉም፡፡ የአብዮታዊ ኤትዮጵያ ፍልስፍናም ይኸው ነበር አሁንም ነው፡፡ታዲያ ሁለቱ ፀጋዮች በዚህ በድህነትና ነፃነት አንድነትና ልዩነት ይስማሙ እንደነበር ነው እኔ የማውቀው፡፡

የአሁኑ ትውልድ ድህነት የሚለው ቃል አይቀበልም ድህነትን ካልተቀበለ ደግሞ ነፃነትን እንደሚያጣ አይገነዘበውም፡፡ አጣብቂኝ ውሰጥ ስለገባ ሊያስብም ሆነ ሊጠይቅ አይፈልግም፡፡ ተስፋ የመቁረጥ አባዜ፡፡ ጥያቄ መጠየቅ ማንን ገደለ? ማንን እንደገደለና ማንን እየገደለ እንዳለ መልሱ ለአንባቢያን እተወዋለሁ፡፡

ድህነት የሚል ቃል በኤትዮጵያ ውስጥ ቦታ ሊኖረው አይገባም ነበር፡፡ የሥነ ልቦና (psychologists) እና የምጣኔ ሀብት (economists) በአገሪትዋ በብዛት አለመኖራቸው በቂ ማስረጃ በሆነን ነበር፡፡እነዚህ ሁለት የአካደሚያ ትምህርት ለኤትዮጵያውያን አስፈላጊ አለመሆናቸውን በባህላችን አኗኗር ታይተዋል፡፡አሁንም ቢሆን የሥነልቦና እና የምጣኔ ምሁራን ለአገሪትዋ ጠንቅ መሆናቸውን ከወዲሁ ለመግለጥ እፈልጋለሁ፡፡የኤትዮጵያ መልክአ ምድርና የአየር ጠባይ ለነዚህ ዓይነት ምሁራኖች ተስማሚ አይሆንምና ነው፡፡ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉ፡፡ ይህ ሌላ አርእስት ስለሆነ ለሌላ ጊዜ ይተላለፍልኝ፡፡

የአብዮቱ ዋና ምሶሶ ሊሆን የታቀደው ኪነት በሚለው ፅንሰ-ሀሳብ ነው፡፡ ኪነት የግል ነው ወይስ የሕዝብ በሚለው ንድፈ-ሀሳብ ታክሎበት ወደ ተግባር ለመተርጎም ነበር የሁለቱ ፀጋዮች ክርክር፡፡ ፈረንጆች Arts and Culture ብለው የሚጠሩትን ለማት፡፡

ሎሬቱና ደብተራው በባህል ላይ የነበራቸው አቃም ልዩነት ፈጠረ፡፡ እንደ ደብተራው እምነት ባህልን መንካት ወይንም ጥሩ ነው መጥፎ ነው ተብሎ ማስተማር የለብንም በራሱ ሀይል ጊዜው ሲደርስ ይለወጣል፡፡ ይከንን የደብተራው አስተሳሰብ በብዙ ኢሕአፓ አባሎችና ደጋፊዎች ሰረፀ፡፡ደርግና ደጋፎዎቹ ሎሬቱም ጭምር የኤትዮጵያን በህል በጉልበት ለመቀየር ተሽቀዳደሙ፡፡ቀውጢ ሆነ፡፡ እልፍ አእላፍ ሕዝብ አለቀ፡፡ በተገላቢጦሽ ግና ኢሕአፓ ባሕልና ሃይማኖት አጠፋ ተብሎ የአባዬን እከክ ወደ እምየ ልክክ ሆነ፡፡

ሰነዶች እንደሚያስረዱት ከሆነ ኪነታዊ ለውጥ ለሁለቱ ፀጋዮች ለየቅል ሆነ፡፡ ይከውም የሎሬቱ ሀሁ በስድስት ወር፤ እናት ዓለም ጠኑ ፐፑ የመሳሰሉትን ማየትና መመርመር ያስፈልጋል፡፡የደብተራው ታሪክና አካሄድ በሰነድ ለማወቅ ከተፈለገ ዴሞክራሲያ፤ዓሲምባ፤ቓራ፡ ገዳማትንና ዩኒቨርሲቲዎችን መጎብኘትንና መመርመር ያስፈልጋል፡፡
የሎሬቱ ትግል ኩረጃ ወይም ኮፒ ሲሆን የደብተራው ደግሞ በግልና በአንድነትን ፈጠራን ማጎናጸፍ ይላል መጸሐፉና ታሪኩ፡፡ ለዚህ ደግሞ ያለተሸራረፈ ነፃነት ያስፈልጋል እያለ ነው ጭሆቱ፡፡

የደብተራው ራዕይና አካሄድ ግና ወያኔም ሆነ ሻዕቢያ እንደ ደርግ ሊቀበሉት አልቻሉም፡፡ምክንያቱም የፍልስፍና ድህነትና፣ የድህነት ፍልስፍና በቅጡ የገባቸው አልመሰለኝም፡፡ለአብዮቱ ተጋልጠን ስለተገኘን እነሆ እስከዛሬ ድረስ እንተራመመሳለን፡፡ ኤርትራውያኖች የፍልስፍና ድህነት ስለሚያጠቃን ኢትዮያውያን ደግሞ የድህነት ፍልስፍና ያጠቃናል፡፡ እኔ ከሁለቱም ስለአለሁበት ነው እኛ እኛ ያልሁት ፡፡ ስለዚህ አርእስተ ጉዳይ የአሁኑ ትውልድ እንዲወያዩበት እጋብዛለሁ፡፡ ስለአለፈው ትውልድ ፍልስፍና ራዕይ ደግሞ የሁለቱን ፀጋዮች ክርክር አቀርባለሁ፡፡

ፀጋዬና ፀጋዬ
ዕለቱንና ሰዓቱን ባላስታውሰውም በለውጡ ዋዜማ መምህር ዓለማየሁ ሞገስ አንድ ሰሚናር በኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቴ ያካሁዳሉ፡፡ የአርዕስቱ ጉዳይም የኢትዮጵያ በዓላትን አስመልክቶ ነበር፡፡ ዋና ቁም ነገሩ ኢትዮጵያ ድሀ አገር የሆነችው የበዓላት ቀን ስለበዙ ነው በሚል ነበር ክርክሩና ሰሚናሩ፡፡ ከ365 ወደ 225 ቀናት በዓላት ስለሆኑ ሕዝቡ ስለማይሠራ ድሀ ሆነ በማለት ሰሚናሩን ከፈቱ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር የሁለቱ ፀጋዮች ራዕይና አመለካከት የተከሰተው ለማለት እደፍራለሁ፡፡

ራዕያቸው አንድ ነው፡፡ ለውጥ ነበር፡፡ አካሂዳቸውንና አመለካከታቸው ግና እዛው ታየና ተሰማ፡፡ ስለ ድህነት መሆኑ ቀርቶ ስለ ለውጥ አካሄድ ጉዳይ ሆነ፡፡ በሌላ አነጋገር ስለ ነፃነት ጉዳይ ሆነ፡፡ ቀደም ሲል አካዳሚያዊ ነፃነት በቅጥር ግቢ ማለት በካምፐስ የነበረው በመንግሥትና በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ትብብር ተሰርዞ ስለነበር ተማሪው በአዲስ አበባ ኳስ ሜዳ እየሄደ ጊዮርጊስ ተሸነፈ አማኑኤል አሸነፈ እያሉ በካምፐስ የተነፈገውን የጩከት ነፃነት በኻስ ሜዳ ለመግለጽ በብዛት ስለሚሄዱ ሎሬት ፀጋዬ ይከንኑ ክስተት ይመለከት ኖረዋል መሰለኝ እንዲህ በሚል ጉዳዩን ገለጠው፡፡

በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር አንድ ድቡልቡል ኳስ በሁለት ባላ ውስጥ ማሳለፍ ነው ብሎ ደመደመው፡፡

በዚህ ጊዜ ደብተራው ደግሞ በተራው ሲናገር የኳሱ ጉዳይ ሳሆን የጊዮርጊስና የአማኑኤል ግጭትና ጭሆት ነው ብሎ ተከራከረ፡፡ ለማነኛውም ለመጀመሪያ ጊዜ ተያዩ ተዋወቁ፡፡ ከዛ በኋላ የሁለቱን ስምና ታሪክ መዘገበው እየመዘገበውም ይገኛል፡፡

“ኢሕአፓ ናፈቀችኝ”
ከፀጋዬ አርአያ ጽሑፍ የተጠቀሰ ነው እንዲህ ይላል “ቀደም ሲል የጠቀስሁት ቁጡ ቀይ ደም በውስጣችን መኖሩን መጠራጠር አይገባንም? በዚህ ዕድሜዬ ማሰብ የማይገባኝ (ምናልባት) አሳብ ድቅን ይልብኛል። በአንድ በኩል ኢሕአፓ ትናፍቀኝ ጀምራለች። ቆራጥነት ማለት በራስም በጠላትም ሕይወት ላይ ውሳኔ ለመውሰድ መወሰን ነው። ኢሕአፓ ናፈቀችኝ። የአባቶቻችን አዋራጆች ልጆቻችንን በጠራራ ፀሐይ የሚረሽኑ፣ አገራችንን በግላጭ የሚሸጡ ወንበዴዎች በየአደባባዩ ሲጐማለሉ ሁላችንም ሊያቃጥለን አይገባም? ኢሕአፓ እንደ ሞተ ዘመድ ናፈቀችኝ። ኢሕአፓ ብትኖር ይኸ ሁሉ ሽፍታ መሪ መንፈሱ አርፎ ከመሸታ ቤት መሸታ ቤት እየዞረ-ሽጉጡን መሬት ለመሬት እየጐተተ-የፈለገውን እያሰረና እያስገደለ፣ በእብሪት ይንቀባረርብን ነበርን? ኢሕአፓን እንዳላማኋት ዛሬ ሙት መንፈስዋን መቀደስ ይዣለሁ።”

ናፈቀችኝ የሚለው ቃል ላለፈውም ለመጪውም ጉዳይ ይሆናል፡፡ ያለፈው ምን ነበር መጪውስ ምን መሆን አለበት?

ያለፈው ነገረ ጉዳዩ ድህነት እንዳልነበረ ሰፊው ሕዝብ ገልጦታል ማስረጃውም የሳይኮሎጂቶችና የኤኮኖሚስቶች አስፈላጊነት አለመኖሩ ነበር፡፡ ጥያቄው የነፃነት ነበር ፀጋዮችም በኪነታቸው ሞያ ጥርት አድርገው ገልጠውልን ነበር፡፡ ድህነት የወያኔዎችና የመሰሎቻቸው ራዕይና መፎክር ሆኖ ቀረ፡፡ የኤትዮጵያ (የኤርትራና ኢትዮጵያ) ሕዝቦች ግን የጠማቸው ነፃነትና ሠላም ነበር፤ ነውም፡፡

ነፃነትና ሠላም እንዴት ይገኛሉ? ሎሬት ፀጋዬና ደብተራው ፀገዬ እንዳስተማሩን

በፊደልና በባንደራ ይገኛል እንጀራ፡፡

አብዮት ከአበየ የሚል ከግዕዝ የተወለደ ሲሆን ዴሞ ማለት ደግሞ ከ ገ/ጋ ተፈልጾ ደግሞ/ደጋግሞ አንድን ክስተት ወደ ዴሞክራቲዘሽን ይቀይራል የሚል ተስፋ ነበር፡: ወያኔ አብዮታዊ ዲሞክራሲያ እያለ ያላግጥ የለ፡፡ለነገሩማ ሻዕቢያ “ሕዝባዊ ግንባር ለፍትሕና ለዲሞክራሲያ” እያለ ያሾፋል እኮ? ቁም ነገሩ በቃላት መጫወት ሳይሆን ፅንሰ-ሐሳቦች በቴዮሪ ተደግፈው ወደ ተግባር ሲለወጡ ብቻ ነው ዴሞክራሲያ የሚያብበው፡፡ የአቶ ማርክስ ግዙፍነት ይከው ነበርና ነው፡፡ ጽንሐተ-ምሁራን ኤትዮጵያውያን ይኅንን በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ለተራ ምሁራኖች ግና ከብዶባቸዋል፡፡

ዘላቂ ያለው መፍትሔ ከተፈለገ ፀገየ ደብተራውን ፈልጎ ማግኘትን ይጠይቃል፡፡ ስለ ድህነትና ነፃነት አንድነትና ልዩነት በዚህ ዓለም ሆነ በሚቀጥለው ያለው ሊነግረን ይችላልና ነው፡፡የአቶ ሙሎጌታ ሉሌ አርአያነታቸውና ምኞታቸው ይህ ከሆነ፤እኔም እጋራለሁ፡፡

ደብተራ አስተማሪ ማለት ሲሆን የኢትዮጵያና የኤርትራ ምሁራኖች ግና እንደ ጠንቃይ አድርገው ያቀርቡታል፡፡ ሳያውቁ ቀርተው ሳይሆን አገር በቀል ስለሆነና ዶላር የማያመጣ እየመሰላቸው ነው፡ቢያውቁበት እሱ ነበር ባለፀጋ የሚያደርጋቸው፡፡ አሁንም መሞከር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ደብተራ ማለትኮ የምሁራን ማዕርግ (scholar) እንደማለት ነው፡፡ ዘመኑ ደግሞ የምርምርና የጥበብ ፍለጋ (research for wisdom) እየሆነ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ደብተራውን ፍለጋ እንሰማራ፡፡

ጥያቄና አስተያየት ካላችሁ
woldetewolde@yahoo.com

No related content found.

Share