ለሀገርህ ስትል አጥብቀህ አስብ

ለሀገርህ ስትል አጥብቀህ አስብ
July 15, 2013
ዳዊት ደመላሽ ( ኖርዌይ )
Madenate.dawit@gmail.com

ኢትዬጵያ አገራችን ስሟ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀስላት በውስጧ ከ 82 በላይ ቋንቋ ያላት ከ 85 ሚሊዬን በላይ እንዳላት የሚነገርላት ከዛሬ 6400 ዘመናት በፊት ጀምሮ የሰው ልጆች እንደሰፈሩባት በታሪክ የሚታወቅ ናት ።

በተለይም በዓለም ሕዝቦች እጅ በሚገኝው መጽሐፍ ቅዱስ እንደጠቀሰው በስልጣኔና በንግድ ዘርፍ እንዲሁም በብልፅግናና በመንግስት ደረጃ ከታወቀች ሶስት ሺህ ዘመናት አስቆጥራለች ። ኢትዬጵያ ከድሮ ጀምሮ የነፃነት ምድር የተረጋጋ ሠላም የሰፈነባት አገር መሆኗ ከባህር ማዶ በተለያየ ጊዜ ችግር በደረሰባቸው ጊዜ መሸሸጊያቸውና መጠጊያቸው ኢትዬጵያ ነበረች።እንዲሁም በአምስተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ ለምሳሌ ያክል ቀደም ባሉት ዘመናት በሐይማኖትና በባሕል የሚመሳሰሉትን ቤተ እስራኤሎች አገራቸው በተለያየ ጠላት ስትወረር ነፍሳቸውን ለማተረፍ ከግብፅ እና የሱዳንን በረሃ አቋርጠው የመጡት ወደዚች ምድር እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ብቻ ሳይሆኑ የትውልዳቸው እርዝራዥ የአካል ምስክር ነው።እንዲሁም በ 5ኛው መቶ ክ/ዘመን በእስያና በአካባቢው በጣኦት አምላኪዎች እንደ ባይተዋር ተቆጥረው ነፃነታቸውን ተገፍፈው ስቃይ በበዛባቸው ጊዜ ከስለትና ከሰይፍ አምልጠው የመጡትን በደስታ ተቀብላ ማረፊያ ቦታ እና የአምልኮ ቦታ መስጠቷ የአቡነ አረጋዊ ደብረዳሞ ገደላቸው ምስክር ነው።እንዲሁም በ 7 ኛው ክ/ዘመንም በመካከለኛው ምስራቅ የእስልምና ሐይማኖት ሲመሠረት በተፈጠረው አለመግባባትና በተነሳው ጦርነት አገራቸው በደም ስትነከር አይተው ተስፋ የቆረጡ መሀመዳውያን ነፍሳቸውን ለማትረፍ አማራጫቸው ኢትዬጵያ ብቻ በመሆኗ ቀይ ባህርን አቋርጠው ሲመጡ በሯን ከፍታ የተቀበለቻቸውና ነፍሳቸውን ያዳነችውና የክፉ ቀን ባለውለታቸው መሆኗን አፉቸውን ሞልተው ይመሰክሩላታል።ይህ ሁሉ የሚያሳየው በቋንቋና በዘር እንዲሁም በሐይማኖት የማታምን አገር መሆኗን ነው በአጠቃላይ ኢትዬጵያ የሠላምና የነፃነት አምባ የሁሉም ነገድ ስብስብ የብሄረሰቦች መገኛ ስትሆን ሕዝቦቿም በቋንቋ በዘር በሐይማኖት በባህል እንቅፋት ሳይሆንባቸው ተስማምተው፣ተቻችለው፣ተሳስበው፣ተፈቃቅረው በጋብቻ ተቀላቅለው የሚገኙባት አገር ናት።

ያለፉት መሪዎቿም በአንድ ኢትዬጵያዊ እንጂ በዘርና በጐሳ የታሰረ መንፈስ ሳያስቀመጡላት ማለፉቸው የማይካድ ሃቅ ነው ዳር ድንበሯን ጠብቀው በኪነ ጥበብ አስውበው ፊደል ቀርፀው የዘመን መቁጠሪያ ቀምረው የማንም ጥገኛ እንዳትሆን አድርገዋት አልፈዋል ግን ይህ እስከ 1983 ዓ/ም ያለው ታሪክ ነው።ከላይ ብዙ የተነገረላትና የተዘመረላት ኢትዬጵያ በ 1983 ዓ/ም የአሁኑ ገዢ መንግስት መንበረ ስልጣኑ ላይ ከተቀመጠ ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ባለው ጊዜ የ 21 ዓመት ጉዞ ውስጥ የብሔራዊ አንድነቷ ፈርሶ ሰላሟ ደፍርሶ ታሪኳ ተበላሽቶ ድንበሯ ተቆራርጦ ክብሯ ተጥሶ የታየበት አሳፉሪ ዘመን ነው።የአሁኑ ገዥ መንግስት የኢትዬጵያን ዳር ድንበር እንደ ባቢሎን ሰዎች ከመግባባት ወደ አለመግባባት ከመፏቀር ወደ መቃቃር ከመከባበር ወደ መናቆር ከአንድነት ወደ ልዩነት ከኢትዬጵያ ህብረት ወደ ክልላዊ ስሜት እንዲያዘነብሉ ያደረገ የጥፋት መንግስት ነው።ይህ መንግስት ቀደም ያሉት ታሪካዊና ወርቃማ ዘመናት በትውልዱ ዘንድ እንዲጠሉ ለማድረግ አነዱን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ በማስመሰል ጥላቻን እየሰበከ ያቀዘቀዘ ብሔርን ከብሔር ጐሳን ከጐሳ በማናከስ ተዋልደው በደም የተሳሰሩትን ደም ያቃባና ያፋታ መንግስት ነው።ለምሳሌ ያህል ጥቂቶቹን እናስታውስ የጋምቤላን ህዝቦች እርስ በእርሳቸው በማጋጨት የኮንሶንና፤የቦረናን ብሔረሰቦችን የጉጂንና፤የደራሳን ብሔረሰቦች በወለጋ የኦሮሞንና፤የአማራውን ህዝብ በማጋጨት በሺህ የሚቆጠሩ ህዝቦችን ያስጨፈጨፈና ያጫረሰ እጁን በደም የታጠበ መንግስት ነው።የቅርብ ጊዜ ትውስታችን እንኳን የሚረሳ አይደለም በ1997 ዓ/ም በተደረገው አገር አቀፍ ምርጫ የሰጠነውን ድምፅ ተነጥቀናል ድምፃችን ይመለሰ በሚሉ ንፁሐን ዜጐች ላይ በጠራራ ላይ በወሰደው እርምጃ ከ 284 ሰው በላይ ህይወት የቀጠፈና የፈሰሰው ደም በተመለካች ህሊና ውስጥ አልደረቀም ።በሐይማኖት በኩልም ብንወስድ ገዥው መንግስት ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በአሰቦት ገዳም በመነኰሳቱና በአካባቢው ህዝብ ላይ የደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋ አርባ ምንጭ ላይ ፕሮቴንስታቱን ከኦርቶዶክሱ በጅማና በኢሉባቦር በስልጤና በጋምጐፋ በማጋጨት የፈሰሰውን ደም ሁሉ በዓይን ላየው ሁሉ መፈጠሩን የሚጠላበት ክስተት ነው ።

እንዲሁም በጅማ ከ 50 ያላነሱ የፕሮቴንስታት ቤተከርስቲያኖች ከነሙሉ ንብረታቸው መውደማቸው የሚታወቅ ነው ።ይህ መንግስት ሙስሊሙን ከኦርቶዶክሱና ከፕሮቴንታንቱ ተፋቅሮና ተቻችሎ እንዳይኖር አንዱነን በአንዱ ላይ እያነሳሳ የሐይማኖት ተቋማትን ሲያቃጥሉ ዳር ቆሞ እሳት የሚሞቅ መንግስት ነው።እነዚህ ተቋማት እርስ አልጋ አልጋጭ ቢሉት እንኳን እርስ በእርሳቸው እንዲጋጩ በውስጣቸው እንዲጋጩ ሙስሊሙን ከሙስሊሙ ኦርቶዶክሱን ከኦርቶዶክሱ ፕሮተንስታንቱን ከፕሮቴንታንቱ በማጋጨት በውስጣቸው በውስጣቸው ሰላም እንዳያገኙ እያደረገ ይገኛል።ከዚህም አልፎ ለዘመናት በነበሩት መንግስታት ተከብሮ የቆየውን የዋልድባን ገዳም በማፈራረስ በውስጡ ቅጠላ ቅጠል እና ፍራፍሬዎች እየተመገቡ ለመላው ዓለም ፀሎት የሚያደርጉ የበቁ አባቶች ይኖሩበት ዋሻ በማፈራረስ መነኰሳቱንም እያሳደደ በእጁ የገቡትን አስሮ እያሰቃየ እና እየገደለ ይገኛል በገዳማቱ ውስጥም የሚገኙትን ቅርሶችንም ያለ ውርስ እየሰረቀና እያጠፋ ይገኛል በዚህ ከቀጠለ በአገራችን ውስጥ ታሪክም ቅርስም ህዝብም ሐይማኖትም ተሟጥጠው ያልቃሉና ውድ የሀገሬ

ልጅ ሆይ ለኢትዬጵያና ለህዝቧ ስትል አጥብቀህ አስብ።
ኢትዬጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!

No related content found.

Share