Category Archives: Articles

የሰላም ትግሉ ያቸንፋል ?

የሰላም ትግሉ ያቸንፋል።
Posted on August 2, 2015 by Eskemeche

የሰላም ትግሉ ያቸንፋል።
አንዱዓለም ተፈራ
እሁድ፤ ሐምሌ ፳፮ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት ( 08/02/2015 )

የሰላማዊ ትግል ተግባራዊነትና ስኬት መለኪያው ምንድን ነው? በዚህ ልጀምር ጽሑፌን። በርግጥ መጀመር ያለበት፤ ሰላማዊ ትግል ምንድን ነው? የት ተተገበረ? እንዴት ተተገበረ? ከትጥቅ አመጹ በምን ተሽሎ ይገኛል? እዚህ ሰላማዊ ትግል፤ እዚያ ግን የትጥቅ ትግል የሚባለው እንዴት ነው? በሚሉት ነበር። ነገር ግን፤ አንባቢዬ በትክክል እንደሚረዱት፤ አሁን የያዝነው፤ በተጨባጩ በሀገራችን ባለው የፖለቲካ ሀቅ፤ ምን ላይ ነው ያለነው? ምን ማድረጉ ለትክክለኛው ሕዝባዊ ድል አመርቂ ውጤት ያስገኝልናል? ከሚለው በመነሳት ነው። እንግዲህ መሠረታዊው መነሻ፤ አሁን ያለንበት የሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ ነው፤ ማለት ነው። እዚህ ላይ ነው እኔ፤ ሽንጤን ገትሬ፤ “ሰላማዊ ትግሉ ያቸንፋል!” በማለት የቆምኩት። እናም ላስረዳ!

ገዥው ወገንተኛ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፣ ከሕዝቡ ተነጥሎ ቆሟል። ሀገራችንን የሚገዛት እንደ ወራሪ ኃይል ሆኖ፤ ፍጹም ፀረ-ኢትዮጵያዊነትን በአደባባይ እየተነፈሰ ነው። ሕዝቡ መሮት በተነሳበት በአሁኑ ሰዓት፤ ዘመናዊ መሣሪያ እስካፍንጫው ታጥቆ፤ በራሱ ምርጥ ሰዎች መንግሥታዊና ግላዊ መዋቅሮች ሰግስጎ፤ የሕዝቡን መነሳሳት በአረመኔነት ለመቅጨት፤ ላይ ታች ይሯሯጣል። ለጋ ወጣቶችን በወገንተኛ ሰበካው በመበረዝ፤ በመዋቅሩ ሰካክቶ አስገብቶ፤ አዲስ ኢትዮጵያዊያን ለመፍጠር እየጣደፈ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም፤ አሰላለፉን አሳምሮ፤ ለዴሞክራሲ አቀንቃኞች ዴሞክራት በመምሰል፤ ለልማት ጎትጓቾች የልማት አራማጅ በመምሰል፤ እንደ ሁኔታው ፊቱን እየኳኳለ ቀርቧል። ካንድ ወዳጄ ጋር ስንጫወት፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር እኮ ውስጡ በስብሷል ለሚለው መልስ፤ ከሚያውቀው የድሮ አባባል መዥርጎ አውጣና፤ “ታዲያ ተወው እንጂ፤ እዚያው ትል ይፍጠር!” አለኝ። ትግሉን የሚወስነው፤ የኛ የታጋዮቹ ሁኔታ እንጂ፤ የምንታገለው አካል አይደለም። ያማ ለሕልውናው የማያደርገው ነገር የለም። እናም በገዥው ማንነትና ተግባር፤ ትግሉ አይወሰንም። ትግሉ የሚወሰነው፤ ይሄን የገዥውን ማንነትና ተግባር በማጤን፤ ታጋዮች በሚያደርጉት ዝግጅትና በሚወስዱት እርምጃ ነው።

የሰላማዊ ትግሉን አስመልክቶ የሚቀርቡት መቃወሚያ መደምደሚያዎች የሚከተሉት ናቸው።

የመጀመሪያው፤ “የሰላማዊ ትግል በሮች ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል!” የሚለው ነው። እንዴ! የሰላማዊ ትግል በሮች ሙሉ ለሙሉ ይዘጋሉ ወይ? ይሄ ምን ማለት ነው። ይህ ለኔ የሚያመለክተው፤ የሰላማዊ ትግሉን ምንነት ከመረዳት ጉድለት መኖሩን ነው። ሰላማዊ ትግል እኮ፤ መስመር ተደርጎ፤ “ከዚህ በፊት ሰላማዊ ትግል፤ ከዚህ በኋላ ሰላማዊ ትግሉ አበቃለት፤ ዛሬ በሩ ተከፍቷል፣ ትናንት በሩ ተዘግቷል እና የትጥቅ ትግል ይጀምራል።” የሚባልበት ክስተት አይደለም። መቼም ይሄን በሚመለከት በተደጋጋሚ የጻፍኩበት ስለሆነ፤ መልሼ አልደርትበትም። የምርጫ ትዕይንቱ መዘጋት፤ የሰላማዊ ትግሉ በር መዘጋት አይደለም። የገዥው ክፍል እንደ እስስት ቆዳው መቀያየሩም እንኳ፤ የሰላማዊ ትግሉን ሂደት አይወስነውም። የሰላሙን ትግል የጀመሩት ሰላማዊ ታጋዮች ናቸው። የትም ሀገር ሆነ በማንኛውም ታሪካዊ ወቅት፤ ሰላማዊ ትግል አድርጉና ቀይሩኝ ብሎ የፈቀደ አምባገነን መንግሥት የለም። ሊያደርገውም የሚፈልግ ሆነ የሚሞክር የለም። በምርጫም አስወግዱኝ ብሎ በሩን ከፍቶ የሚያስተናግድ አምባገነን መንግሥት አልተፈጠረም። በምርጫ የሚያምንና ያን የሚያደርግ፤ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ነው። ያን መንግሥት ለመቀየር ደግሞ፤ ሰላማዊ ትግል አይደረግም። ውድድር ማድረግ ብቻ ነው። ኑሮ ግድ ብሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ ስቃይ ውስጥ ሲከተው፤ መንግሥት የሕዝቡ አገልጋይ መሆኑ ቀርቶ ሕዝቡ የመንግሥቱ አገልጋይ እንዲሆን ሲደረግ፣ መንግሥቱ ጠባብ፣ ወገንተኛና አምባገነን ሲሆን፣ ታጋዮች እምቢ ብለው ተነሱ። በሰላም የመታገሉን ፈቃድ ከማንም አላገኙም። ፈቃጁም ሆነ ሰራዡ ታጋዮቹ ናቸው። የሰላማዊ ትግሉንም በር የሚዘጉት፤ ሰላማዊ ታጋዮች፤ አሁን ግባችንን መትተናል፤ ካሁን በኋላ ሰላማዊ ትግሉ አበቃ ብለው፤ እጃቸውን ሲያነሱ ብቻ ነው። በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ቀን ከሌት የሚሰቃዩት ኢትዮጵያዊያን ይሄን አላሉም፤ አይሉምም፤ ስቃያቸው እስካላቆመ ድረስ!

ሁለተኛው ደግሞ፤ የገዢውን ቡድን የአድራጊ ፈጣሪነት ሚና አግዝፈው፤ በሁሉም ቦታ አለ፣ ሕዝቡን አስሮ ይዟል፣ አንድ ለአምስት በመጠርነፍ መፈናፈኛ አሳጥቷል፣ በምንም መንገድ ለሰላማዊ ትግሉ ቀዳዳ አይሠጥም የሚባለው ነው። በተጨማሪ ደግሞ፤ እኒህ ገዥዎች በዚሁ ያለፉበት ስለሆኑ፤ “ማንኛውንም የአደረጃጀት ሂደት ስለሚያውቁት፤ ከሕዝቡ ቀድመው ሁሉን ያውቁታል!” እናም “በምንም ዓይነት መንገድ ከዚህ መንግሥት ውጪ መደራጀትና ማደግ አይቻልም!” የሚባለው ነው። እንዴ! ሕዝቡኮ ከገዢው ቡድን ይበልጣል፣ ይበዛል፣ ይልቃል፣ ያውቃል። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ዕድሜውን ሊያራዝም የሚችለው፤ ሕዝቡን በማሰቃየት፣ በማግለል፣ በማሰር፣ ካገር በማባረር፣ በጣም ጥቂቶቹን ከአብዛኛው በማስበለጥና ወገንተኛ በመሆን ነው። ይህ ደግሞ ከሞላ ጎደል ኢትዮጵያዊያንን በያሉበት በድሏል፣ አስቆጥቷል፣ አነሳስቷል። ስለዚህ፤ በምንም መንገድ ቢሆን፤ የአምባገነኑ ወገንተኛ ገዢ ቡድን ማንኛውም ጥረት፤ ከሕዝቡ የኑሮ ስቃይ እውቀት አይበልጥም። ሕዝቡ እየተፈተነ ያለው፤ በመሞትና በመኖር መካከል ነው። ሌላ ምርጫ የለውም። በየዕለቱ በአምባገነኑ ቡድን በሚደርስበት በደል ዙሪያ በሚደረጉ አመጾች፤ ሕዝቡ አቸናፊ ይሆናል። ሌላው የድርጅቶች ድርሻ ነው።

ሶስተኛው ደግሞ፤ “አሜሪካ፣ አውሮፓና ቻይና ስለሚደግፉት፤ በምንም መንገድ፤ በሰላማዊ ትግል ገዢው ቡድን አይወድቅም!” የሚለው ነው። እንዴ! መቼ ነው ለውጭ ሀገር መንግሥታት፤ እጃችንን አራግበን፤ ያውላችሁ እንደወደዳችሁ ብለን፤ የሀገራችንን የትግል ሂደት ወሳኝነት ቦታ የሠጠናቸው? እኛው ሠጪና ነሺ ከሆን ደግሞ፤ በጃችን ያለውን ወሳኝነት፤ እንዴት አድርገን ነው የነሱ ነው የምንለው! ትናንት በኤርትራ ጉዳይ፤ እኒሁ ምዕራባዊያን፤ ከጣሊያን ጋር አብረው መቆማቸውን ረሳን እንዴ! ቻይና እኮ ከማንም የባሰች አፋኝ ሀገር ናት! ከሷ ምን ይጠበቃል! የኛን የኛ እናደርገው።

አራተኛው ደግሞ፤ “ሕዝቡ አንድ አይደለም። ሕዝቡ አልተነሳም። ሕዝቡ ባልተነሳበት ወቅት፤ ሰላማዊ ትግሉ አይሠራም።” የሚለው ነው። እንዴ! ደግሞ በሕዝቡ ማሳበብ ጀመርን! ሀቁንማ መቀበል ያስፈልጋል። ደግሞስ ሕዝቡ ለሰላማዊ ትግሉ ካልተነሳ፤ እንዴት ብሎ ነው ለትጥቅ አመጹ የሚነሳው? ሕዝቡ ከድርጅቶች ደጋግሞ ቀድሞ ተገኝቷል። አሁንም ከድርሻው በላይ መስዋዕትነት እየከፈለ ነው። ከዚህ በላይ ሕዝቡ ምን ያድርግ? የፖለቲካ ድርጅቶች ማድረግ ካለባቸው በላይ ጋዜጠኞች ፍዳቸውን እያዩ አይደለም! ሕዝቡ ለምን ሠረታችሁ ተጠቀማችሁ በመባል ንብረታቸው እየተነጠቀ አይደለም? ይሄን ሕግ አላከበራችሁም፣ ዓይናችሁ አላማረንም አየተባሉ አየተጎሳቆሉ አይደለም? ሕዝቡ ያለድርጅትና ያለመሪ ሀገሩን ነፃ የሚያወጣ ከሆነ፤ የታጋዮች አስፈላጊነት የቱ ላይ ነው? ሕዝቡንስ አንድ ለማድረግ፤ በአንድነት ትግል ማካሄዱ አይበጅም!

እውነቱን እንቀበል! የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ከሁሉ በላይ የሚፈራው ነገር ቢኖር፤ የሕዝቡን አንድነት ነው። የሕዝቡን ሰላማዊ አመጽ ነው። ታጋዮች ሕዝቡን እንዳያገኙ ያላደረገውና የማያደርገው ነገር የለም። በዚህ መንግሥት እምነት፤ ታጋዮችን ከሕዝቡ ነጥሎ በማሰር፣ በማባረርና በመግደል፤ ሰላማዊ ትግሉን የሚገታ መስሎት ተያይዞታል። ነገር ግን፤ ሰላማዊ ትግሉን የሚያራምዱት የሕዝቡ አካል ናቸው። አንዱ ሲታሰር በሕዝቡና በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መካከል ባለው ቅራኔ የተጸነሱ፣ በሕዝቡ ብሶት የተፈለፈሉ፤ ሌሎች በብዛት እየተከተሉት፤ የበለጠ ውጥረት ውስጥ ከተውታል። ሰላማዊ ትግሉም የመብራት አጥፊና አልሚ ቁልፍ የሚቆጣጠረው፤ አንዴ የሚበራ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚያጠፋ አምፖል አይደለም። ምንነቱ በሆነው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ባህርይ የተቀረጸ የሕዝብ አመጽ ነው። ሰላማዊ ትግሉ ከሕዝቡ ብሶት ጋር የተቆራኘ ክስተት ነው።

ይልቅስ በሰላማዊ ትግሉ ዙርያ አመርቂ የሆነ ውጤት ለማምጣት፤ በአንድነት አብረን እንነሳ። በሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ የሚታዩ፤ ከፋፋይ የሆኑ፤ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ይሄን ማስወገጃው በአንድነት መነሳቱና፤ አሁኑኑ በገዥው መንግሥት ላይ ጫና ማድረጉ ነው። የየራሳችን ፓርቲዎች ከምንል፤ የአንድነት እንቅስቃሴ እንበል። ማለቱ ብቻ ሳይሆን ደግሞ፤ በሕዝብ ፊት የሚታይ የአንድነት ጥረት እናድርግ።

የሰላማዊ ትግሉ በአንድ ድርጅት ብቻ የሚመራ ነው። የሰላማዊ ትግሉ ትኩረቱ፤ ያለውን ሥርዓት ለመለወጥና ትክክለኛ የሕዝቡ ተወካይ መንግሥት የሚኖበትን ሂደት ለመፍጠር ነው። የምንታገልላቸው ዕሴቶቻችን፤ የኢትዮጵያዊያን አንድነት፣ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበር፣ የሕግ የበላይንት መስፈንና የያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ናቸው። በነዚህ መሠረታዊ መታገያ ዕሴቶቻችን ዙሪያ፤ በውጭ ሀገር ያለነው ኢትዮጵያዊያን ብንሰባሰብ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ሰላማዊ ትግል ትልቅ ብርታት እንሠጣለን። አስተዋጽዖችንም ትርጉም ይኖረዋል። ተከታዩም አስተማማኝ ይሆናል። አዎ! ላለፉት ከሃያ በላይ ዓመታት የትብብሩን ጥሪ ስናስተጋባና አንዲትም እርምጃ ወደፊት ሳንሄድ ኖረናል። ይህ ግን የትብብሩን አስፈላጊነት በምንም መንገድ አይቀይረውም። ጥረታችንን በተስተካከል መንገድ ማካሂያድና ጥበብ በተሞላበት መንገድ መምራት ነው። አሁን በአንድ ተነስቶ መታገሉ አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው። ያ ካልሆነ፤ ትግሉ የእሬያ ታጥቦ ጭቃነት ነው። አንድነቱን ገሃድ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ያለ ክፍል መኖሩን ተገንዝቤያለሁ። በርቱ እላለሁ።