Category Archives: Comments

አስታያየቶች

እንኳን ለ42ኛዉ ዓመት የኢሕአፓ ምሥረታ በሰላም አደረሰን – ከበቀለ ገሠሠ

ለዉድ የኢሕአፓ አመራርና አባላት በሙሉ
እንኳን ለ42ኛዉ ዓመት የኢሕአፓ ምሥረታ በሰላም አደረሰን
ከበቀለ ገሠሠ

እኛ በተዓምር ተርፈን ይህን ታላቅ ዕለት ለመዘከር ብንበቃም ከመቶ ሺሆች በላይ የሆኑ ንፅሃን ወጣቶቻችንና ዜጎቻችን በጨቋኝ ፋሺስቶች እጅ ታስረዉ፤ ተደብድበው፤ ተሰቃይተዉና ተረሽነው እንደረገፉ ከማስታወስ ጋር ነዉ። እነዚያ አገራችን ያፈራቻቸዉ እጅግ የነቁ ብሩሃን ወጣቶች በዚያ አረመኔያዊ መንገድ የረገፉት፤ ከዚያም የተረፉት ደብዛቸዉ ጠፍቶ የቀሩት ምንም ኃጢአት ሠርተዉ አልነበረም።

ትግላቸዉ ለግል ሥልጣንና ጥቅም አልነበረም። ያንን ሁሉ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉት አስፈላጊዉን የወቅቱን ታሪካዊ ሃላፊነት በመሸከማቸዉ ብቻ ነበር።
ገበሬዉ መሬት አጥቶ በጪሰንነት ሲመዘበር፤ ሲሰቃይና ሲሞት ዐይቶ ‘ለመሬት ላራሹ’ ብሎ መታገል ፅድቅ እንጂ ኩነኔ አልነበረም።

ህዝባችን ከፍጹም ባላባታዊ ሥርዓት ተላቅቆ ዲሞክራሲን እንዲጎናጸፍ መጠየቁ ፅድቅ እንጂ ኩነኔ አልነበረም። የተጨቆነዉ ህዝባችን ከወታደራዊ አምባገነን ተላቅቆ ህዝባዊ መንግሥትን እንዲመሠርት መታገሉ ፅድቅ እንጂ ኩነኔ አልነበረም።

በኢሕአፓ ሥር የተሰለፉት ንፁሐን ዜጎች ህዝባችንን ለሥልጣን እንዳያበቁ ብዙ ዉስጣዊና ዉጪያዊ ጠላቶች ተረባረቡባቸዉ፤ የዉስጦቹ ጠላቶች ለሥልጣንና ለግል ጥቅም ሲሆን የዉጪ ጠላቶች የነፃነት ምሳሌ የሆነችዋን አገራችን ለማፍረስና ኩሩ ህዝባችንን ለማዋረድ ነዉ።

አሁንም የህዝብ ነፃነት እስከሚገኝ ድረስ የተቀናጀ ትግል መቀጠል አለበት፤ ቁልፉም የኅብረት ትግል ነዉ። የህብረት ትግልን ያልፈለጉት ወገኖች አገራችንን ለክፉ ጭቆናና እንግልት እንደዳረጉ በመገንዘብና ከስህተቶቻቸዉ በመማር ውድ አገራችንን ከጥፋት የማዳን ግዳጅ ይጠበቅባቸዋል።

ቸሩ አምላካችን እጅግ ለተቸገረዉና ለተሰቃየዉ ህዝባችን ይድረስልን፤ ውድ አገራችንን ጠብቆ ለዘለዓለም ያኑርልን፤ አሜን