Author Topic: የኢሮብ ሕዝብ የድረሱልኝ ጥሪውን እያስተጋባ ይገኛል  (Read 3472 times)

staff3

  • Global Moderator
  • Newbie
  • *****
  • Posts: 260
የኢሮብ ሕዝብ የድረሱልኝ ጥሪውን እያስተጋባል ይገኛል
የኢሮብ መብት ተሟጓች ማህበር (ኢመተማ) ጥሪ ለ፦
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ
ኢትዮዽያ መንግስት
ኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት
ኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች
ኢትዮጵያ የሲቪክና ሙያ ማህበራት

ኢመተማ ድምጽ አልባ ለሆነው ለኢሮብ ህዝብ መብት ለመሟገት የተቋቋመ የሲቪክ ማኅበር ሲሆን በኢትዮጵያ ሁሉንም ባለ ድርሻ ያለ ምንም አድልዎ በእኩልነት ለማስተናገድ የሚችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን በሚደረገው ትግል የበኩሉን ድርሻ የማበርከት ዓላማ ያለው ማኅበር መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ለማድረግ ይወዳል። ከዚህም በተጨማሪ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ፊት ለፊት አፍጦ የመጣውና የኢሮብ ብሔረ-ሰብ ህልውና እጅጉን የተፈታተነው የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ውዝግብ ተብሎ የሚጠራውን የድንበር ጉዳይና ከወረራው ዕለት ጀምሮ በየጊዜው ውዝግብ
ከተፈጠረባቸው የኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበሮች በሻዓቢያ እየታገቱ ተወስደው መዳረሻቸው ስላልታወቀው ኢትዮጵያዊያን በርከት ያሉ መግለጫዎችን ሲያወጣ ቆይቷል። ሆኖም እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ጆሮ የሰጡንና ጮኸታችንን የሰሙን ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከሚጠበቀው በታች ሆኖ አግኝተነዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ ጭራሽ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎናል።

የአገር ጉዳይ የጋራ ጉዳያችን ነውና የምንመሰጋገንበት ባይሆንም ከፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ፤ ጩኸታችንን አድምጦ ላስተጋባልንና የድንበር አከላለልን አስመልክቶ የአልጀርሱን ስምምነት እንደማይቀበለው በፕሮግራሙ ውስጥ በግልጽ ያስቀመጠውን “ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ”ን ለማመስገን እንወዳለን። ከመገናኛ ብዙሀን ደግሞ ምን ጊዜም ለጮኸታችን ዋጋ በመስጠት ያለ ማወላወል ሁሉም መግለጫዎቻችንን በማስተናገድ አገራዊና ህዝባዊ ግዴታቸውን የተወጡትን, እነ http://www.ethiomedia.com የመሳሰሉትን ድረ-ገጾችን እያመሰገን ሌሎች ድረ-ገጾችም የነሱን አርአያ ተከትለው የምናወጣቸው መግለጫዎችን እንዲያስተናግዱ፣ እንጠይቃለን። እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ነገሩ የአገርና የህዝብ ጉዳይ ስለሆነ፣ የኢሮብ ብሔረሰብም የኢትዮዽያ ህዝብ ኣካል ነውና ትኩረት እንድያደርጉበት ጥርያችንን እናቀርባለን።

ወደ ዋናው ጉዳያችን ከመግባታችን በፊት ኢሮብ የሚባል ህዝብና አከባቢ የት እንደሚገኝ ለማያውቁት ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን
ትንሽ ማብራሪያ እናስፍር። ኢሮብ በሰሜን ኢትዮጵያ በሰሜን ምሥራቅ ዓጋመ ውስጥ የሚገኝ አከባቢ ነው። ይህ አከባቢ የኢትዮጵያ
ታሪክ ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ከኢትዮጳያዊነት ውጭ የሆነ ታሪክ የሌለው ከመሆኑም በላይ የኢሮብ ህዝብ የውጭ ወራሪ ጠላት
በመጣ ቁጥር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከወገኑ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ተሰልፎ በጀግንነት ከጠላት ጋር ተናንቆ የተዋደቀ ህዝብ
መሆኑ ታሪክ የማይዘነጋው ሀቅ ነው። ከዚህም አልፎ የአብዛኛዎቹ የውጭ ወራሪዎች መግቢያ በር ላይ በመገኘቱ ምክንያት የመጀመርያ
የወረራዎች ገፈት ቀማሽ እየሆን እስከዚች ቀን የደረሰ ህዝብ ነው። የሩቁን ትተን በ1990 ዓ.ም የሻዓቢያ ወረራ በተፈጸመበት ጊዜ፤
መሣርያ ከጠላት እየነጠቀ ያደረገው ጀብዱ የመከላከል ጦርነት (ዕጡቃት-ሰንበት) እንደ ምሳሌ መጥቀሱ አገባብ ይሆናል።
የኢሮብ ህዝብ ዛሬ እንደ ብሔረ-ሰብ ህልውናው በጣም አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ
የመጣው መኖሪያ ቀየው ዛሬ በአልጀርስ ስምምነት ተወጥኖ በሄግ ውሳኔ ጸድቆ በዚህ ድረ-ገጽ ከመግለጫው ግርጌ የሰፈረው ካርታ
እንደሚያመለክተው ለም ከሆነው የመሬቱ አንድ ሶሰተኛ ለወራሪው የሻዓቢያ አገዛዝ እንዲሰጥ ተበይኖብናል ተብሏል። (ካርታውን
ለማየት http://www.irobmablo.org/IRAA_Statement_May26.pdf ይህንን አድራሻ ይጫኑ።) የኢሮብ ብሔረ-ሰብ አዶሓ ኢሮብ
(ሶሰት ኢሮብ) በሚል መጠሪያ የሚታወቅ፤ ሓሳባላ፤ ቡክናይቲ-ዓረና አድጋዲ-ዓረ የሚያጠቃልል ሲሆን፤ በአልጀርስ ስምምነት መሰረት
የተሰጠው የሄግ ውሳኔ ተግባራዊ ከሆነ በተጠቀሰው ካርታ እንደተመለከተው ለም የሆኑ የቡክናይቲ-ዓረ ሰፊ ቀበሌዎችን ጨምሮ
መላው አድጋዲ-ዓረ ወደ ኤርትራ እንደሚካለል ግልጽ ነው። ይህ ማለት ወደ ኤርትራ በሚካለለው ግዛት ውስጥ የሚኖረው ህዝብ
በአንጻራዊ መልኩ ሲታይ የአዶሓ ኢሮብ ግማሽ በመሆኑ ይህ ብሔረ-ሰብ በሁለት አገሮች መካከል ተከፍሎ ለመጥፋት የተወሰነበት
ከመሆን ተለይቶ ለመታየት ፈጽሞ የሚቻል አይሆንም። በመሆኑም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ጥፋት ለመታደግ የሚቻለውን ሁሉ

እንዲያደርግ ዛሬም እንደትላንቱ ጥርያችንን ለማቅረብ እንገደዳለን። ይህንን ጥሪ ደግመን ደጋግመን ለማቅረብ የምንገደደው አብዛኛው
ኢትዮጵያዊ ወገናችን ከኢትዮጵያ ለኤርትራ ስለሚለገሰው መሬት ያለውን ብዥታ ለመቅረፍ ይረዳል ከሚል እሳቤ በመነሳት መሆኑ
ልብ ሊባልልን እንፈልጋለን።

ዛሬ ከኢትዮጵያ ለኤርትራ ስለተበየነው ግዛት ሲወሳ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊ ምሁራን በሚጽፏቸውና ለመገናኛ ብዙኃን በሚሰጧቸው
ቃለ-መጠይቆች ውስጥ ሲጠቅሱት የምናነበውና የምናዳምጠው በአብዛኛው ስለ ባድመ ነው። ስለባድመ መወሳቱና መከራከሩን
የኢትዮጵያ ግዛት ነውና የምንሰማማበት ይሆናል። ሆኖም እዚህ ላይ የተጠቀሱ የኢሮብ መሬቶችና ሌሎች ለኤርትራ የተከለሉ
የኢትዮጵያ ግዛቶችም ቢጨመሩበትና የኢትዮጵያ ህዝብ ለወራሪ ለመሸለም ለድርድር በመቅረብ ላይ ስላሉ ሉዓላዊ ግዛቶቹ እንዲያውቅ
ቢደረግ መልካም እንደሚሆን ክልብ እናምናለን። የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢሆን ከባድመ ውጭ ለኤርትራ ስለተሰጡት ሌሎች
ግዛቶቻችን ሲናገርም ሆነ የአከባቢዎችን ስሞች ሲጠቅስ አይሰማም። ይህ ያለምክንያት ነው የሚል እምነት የለንም። ከአከባቢው ነዋሪ
ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ አከባቢውን ስለማያውቀው የትኛው ቀበሌ የኢትዮጵያ የትኛው ደግሞ የኤርትራ እንደሆነ ለማወቅ
አይቻለውም። በመሆኑም በደፈናው ከዚህ በፊት በአቶ ሥዩም መስፍን በይፋ እንደተነገረን “በጦር ሜዳ የተጎናጸፍነውን ድል በዓለም
ዓቀፉ ፍርድቤትም ደግመነዋል” የሚለውን “በጦር ሜዳ ያስመዘገብነውን ድል በድርድር ደግመነዋል” በሚል ባዶ መፈክር እንዳይተካ
እንሰጋለን። ሆኖም እኛ የአከባብው ተወላጆች ነንና እንኳን መላውን አድጋዲ ዓረና ለም የሆኑ የቡክናይቲ ዓረ መሬት እያንዳንዷን
የራሳችን የሆነች ዛፍና ማሳን እናውቃታለን። ስለሆነም፤ የአከባቢያችን የኢትዮጵያ ግዛቶችን በሚመለከት የኢትዮጵያ ህዝብ ዳር
ድንበሩን እንዲያውቅ የማድረግ ሓላፊነት አለብን ብለን እናምናለን። ስለሆነም፤ ኢትዮጵያውያን የመጀመርያ የሻዓቢያ ወረራ ሰለባ
የሆነችው ባድመ በዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን ትኵረት በማግኘቷ የዚች ግዛት ወደ ኢትዮጵያ የመከለልና ያለመከለል እጣ የሌሎች
ሰፊ ግዛቶቻችን እጣ ፈንታን ጋርዶት በነዋሪው ዜጋ ብዛት ከማንም ካልበለጡ የማይተናነሱ ግዛቶቻችን “በዓይንህን ሸፍን ላሞኝህ”
ዓይነት ተራ ፈሊጥ እንዳንሞኝ መልሰን መላልሰን ለማሳሰብ እንወዳለን። “እንኳን መሬታችን በሆነ ምክንያት የመሬታችን ድንጋይ ወደ
ኤርትራ ግዛት ቢሄድ ሞተንም እንመልሷለን” የሚለን አንድ ኵሩ ኢትዮጵያዊ ህዝብ የወገኑን ድጋፍ የመሻት መብት አለው ብለን
እናምናለን።

እንደገና ስለ ድንበር ጥያቄ ለማንሳት የሚገፋፉን ምክንያቶች በርካቶች ናቸው። ከነዚህም ውስጥ በቅርቡ አቶ በረከት ስምዖን በአንድ
የኤርትራዊያን ‘የፓልቶክ’ መወያያ መድረክ ባደረጉት ንግግር ባድመ የኤርትራ ናት ማለታቸው፣ ቀጥሎም ጠቅላይ ሚኒስትር
ኃይለማርያም ደሳለኝ ለአልጀዚራ ተሌቪጅን ጣቢያ የሰጡት ቃለ-ምልልስ በዋናናት ሊጠቀሱ የምችሉ ናቸው። የቀድሞው ጠቅላይ
ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ አሰና ለሚባለው የኤርትራ ተቃዋሚዎች ደጋፊ ሬዲዮ ጣቢያ የሰጡትን የኢትዮጵያ ግዛቶችን በድርድር
ለሻዓቢያ ለማስረከብ ዝግጁነታቸውን ያበሰሩበትን መግለጫ አስመልክቶ መኢተማ በወቅቱ የተቃውሞ አቋሙን የገለጸበት መግለጫ
ማውጣቱ የሚታወስ ነው። ዛሬ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ “አስመራ ሄደህ ከአቶ ኢሳያስ ጋር ትደራደራለህ ወይ
ብለሽ ከጠየቅሽኝ፤ መልሴ አዎ ነው” በማለት ያልተጠየቁትን ከመመለሳቸውም በላይ ከዚህ በፊትም አቶ መለስ ዜናዊ አስመራ ድረስ
በመሄድ ለመደራደር ከሃምሳ ጊዜ በላይ ጥያቄ አቅርበው እንዳልተሳካላቸው በይፋ አሳውቀውናል። በተጨማሪም የአቶ መለስን ፖሊሲ
ሳይበረዝ እንዳለ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ነግረውናል። አቶ መለስ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ዙርያ የነበራቸው አቋም ደግሞ
ምን እንደነበረ ሁሉም በግልጽ የሚያወቀው ስለሆነ እዚህ ላይ መድገሙ አንባቢን ማሰልቸት ይሆንብናል። ሆኖም የዛሬ ከትላንትናው
ለየት የሚልበት ሁኔታ እየተከሰተ እንዳለ እንገነዘባለን። ይኸውም አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ትላንት በአፍንጫየ ይውጣ ሲሉ እንዳልነበረ
ሁላ ዛሬ ከኢትዮጵያ ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ስለ ድንበር መካለል ለመሸማገል ዝግጁ ነኝ ማለታቸውንና ከዛም አልፈው ኳታር
በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር መካለል ጉዳይ እንድታደራድራቸው መጠየቃቸው ዓዋተ የተባለው የኤርትራዊያን ድረ-ገጽ ዘግቦት ይገኛል።
ስለሆነም ኢመተማ ነገሩ ሁሉም የሀገራችን ዳርድንበርና በድንበሩ የሚኖሩ ዜጎች ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች የዳር ድንብር ጥያቄ
ከምን ጊዜም በላይ ነቅተው እንዲከታተሉት በሚገባ ወቅት ላይ ነን ብሎ ስለሚያምን ነው ይህን ጥሪ አሁን ለማቅረብ የፈለገው። ከዚህ
በፊት ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማደራደር በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ገልጻ ነበር። ሆኖም፤ የማደራደሩን ሓሳብ ምን ላይ
እንዳደረሰችው ወይም በምን ምክንያት እንዳቋረጠችው ሳይታወቅ አሁን ኳታር ሸምጋይ ለመሆን እንደተጠየቀች መወራት ጀምሯል።
ወሬው ትክክል ከሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግሥት ምን አቋም እንዳለው ለመስማት እንጓጓለን። በነገራችን ላይ
ኢትዮጵያና ኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ኳታር ከሻዓቢያ ጋር በነበራት ግንኙት ምክንያት አቋርጠው እንደነበር የሚታወቅ
ነው። ዲፕሎማሲያዊ ግንኑነታቸውን ያደሱት አሁን በቅርብ ቀናት መሆኑም ይታወቃል። የሆነ ሆኖ ነገሩ በይፋ ሲወጣ የምንለው
ሊኖረን ስለሚችል ለጊዜው እዚሁ ላይ ለመግታት መርጠናል። ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመለስ ግን ከማንም ጋር ለህዝቦችና አገሮች ሰላም
ሲባል የሚደረገውን ሽምግልናና ድርድር የሚደገፍ ቢሆንም፤ የአንድን አገርና ህዝብ ጥቅምን የሚጎዳና የአንድን ብሔረ-ሰብ ህልውና
የሚፈታተን ድርድር ውስጥ መግባት የሚያስከትለውን አደገኛ መዘዝ ምን ሊሆን እንደሚችል የአልጀርስ ስምምነት በሚገባ
አስገንዝቦናል። አቶ ኢሳያስ በብልጠታቸው ይሁን በአፍቃሬ ኤርትራ አስመሳይ ባለጋራዎቻቸው ይሁንታ፧ በኢትዮጵያ ልጆች ደም
የተከበረውን በወረራ ይዘዋቸው የነበሩ ግዛቶቻችንን አልጀርስ ላይ በወርቅ ሳህን ቀርቦላቸው በፈረሙት ውል መሠረት ከአገባብ ውጭ
የተወሰነላቸውን የሰው ግዛት ካልተረከብኩ በማለት ዘራፍ በማለት ላይ እንደነበሩ ሁላችን የምናውቀው ጉዳይ ነው። አሁንም አቶ
በረከት በአንድ የኤርትራዊያን ‘ፓልቶክ’ ክፍል ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ባድመ የኤርትራ ነው በማለት የሰጡት ቃል አቶ መለስ “አንድ

ቤት ለሁለት እንዳይከፈል” መደራደር አለብን በማለት ሲያራምዱት ከነበረው አቋም ጋር ተዳምሮ ሲታይ አዲሱ ድርድር ጥያቄ
በ’ኖርማላይዜሽን’ ተሳቦ ግዛቶቻችንን የሚያስረክብ እንዳይሆን ስጋቱ አለን። ያም ሆነ ይህ የኢሮብ ሕዝብ ይህንን ለመቀበል በምንም
ዓይነት መንገድ ዝግጁ እንዳልሆን ጠላትም ሆነ ወዳጅ ሁሉ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን።

ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ
ዳር እየተቆረሰ ሲጠፋ ማኸል ዳር ይሆናል እንደሚባለው፤ ከኤርትራ ጋር የሚዋሰኑ የኢትዮጵያ ግዛቶች ለሻዓቢያ ሲለገሱ ዝም ብለን
መመልከቱ ማኸሉን ዳር ወደ ማረግ እየተጠጋን መሆኑ ታውቆ የድንበራችንን ጉዳይ በአንክሮ ሊከታተለው እንደሚገባ ይገነዘበዋል
ብለን እናምናለን። የተጠቀሰውን ድንበር ለማስከበር ብርቅየ ልጆችህን ገብረህበታል። ያም አልበቃ ብሎ፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት
አናሳ ብሔረ-ሰቦች አንዱ የሆነው የኢሮብ ብሄረሰብ ወገንህ ለሁለት ተከፍሎ ህልውናው አደጋ ላይ የወደቀበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ
የድረሱልኝ ጥሪውን እያስተጋባልህ ይገኛል። ስለሆነም ለዚህ ወገንህና ውድ ልጆችህ ክቡር ህይወታቸውን ለገበሩለት ሉዓላዊ መሬትህ
ዘብ እንድትቆም፣ ካላንተ ሁለገብ ተሳትፎ የሚደረገ ማንኛውም የዳር ድንብር ማካለል ሆነ ድርድር ተቀባይነት እንደሌለው በሚቻለው
መንገድ ሁሉ መንግሥትን እንድታስታውቅና እንድታስጠነቅቅ ጥርያችንን እናቀርባለን።
የኢትዮጵያ የሙያና ሲቪክ ማህበራት፤
ዛሬ በሕወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት በወጣው አዲሱ ‘ሕግ’ ምክንያት ህልውናቹህ ፈተና ውስጥ መውደቁ የሚታወቅ ነው። ሆኖም
ለህልውናቹህ መከበር ከምታደርጉት ትግል ጎን ለጎን ይህንን በአገር ዳር ድንበር የሚደረገውን ግልጽነት የጎደለው የድብብቆሽ ድርድር
መደረግ እንደሌለበት በማመላከት የትግላቹህ አካል አድርጋቹህ እንድትንቀሳቀሱበት፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ ጠረፍ አከባቢ
የሚኖረው ህዝባችን ሁኔታም በቅርበት እንድትከታተሉት በትህትና እንጠይቃለን።
ጥሪ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍንባትና አንድነቷ እንዲጠበቅ የምትዋደቁላት አገርና ህዝብ ከዳር እስከ ዳር በአንድ ዓይን ታዩታላቹህ
ብለን እናምናለን። በመሆኑም፤ አሁን ከሚታየው ሁኔታ አንጻር በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ይደረጋል ተብሎ በመናፈስ ላይ ያለው
የድርድር ዜና እጅጉን የሚያሳስበን መሆኑ እንድትረዱልን እንሻለን። ስለ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ጉዳይ ሲነሳ ሁሉም ቀድሞ
የሚያነሳውም ስለ ባድመ ብቻ መሆኑ ሌላውን አከባቢ እንደተዘነጋ ሆኖ እንዳይታይ ስጋት ይፈጥርብናል። በመንግሥት ለመጥቀስ
የማይፈለጉ እንደ አድጋዲ-ዓረ የመሳሰሉ የኢሮብ ሰፊ ግዛቶች ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ በሄግ ውሳኔ ወደ ኤርትራ መካለላቸው በግልጽ
ተቀምጦ የሚታይ ጉዳይ ነው። የሕወሓት/ኢህአዴግ መንግሥትም የሄግ ውሳኔን እንደተቀበለው በይፋ እየነገረን ነው። ስለሆነም፤
በድርድር ስም ለኤርትራ የሚለገሰው ግዛታችን የኢሮብ ብሔረ-ሰብን ለሁለት ከፍሎ የሚያጠፋ ከመሆኑም በላይ በአከባቢው ዘላቂ
ሰላም እንዳይኖር እንቅፋት ሆኖ እንደሚዘልቅ አይቀሬ ክስተት ነው። በመሆኑም፤ በዚህ የዳር ድንበር ጉዳይ ላይ ያላቹህን አቋም ግልጽ
በማውጣት፤ ይህንን አገርንና ወገንን ለዘለቄታው የሚጎዳ ድርድር በይፋ እንድትቃወሙት ጥርያችንን እናቀርባለን።
ለኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት፤

ሉዓላዊ ዳር ድንበርን ለማስከበር መተኪያ አልባ የሆነች ህይወትህን በመክፈል ወረራውን በጀግንነት ቀልብሰሃል። እነዚህን ዛሬ
ለድርድር በመቅረብ ላይ የሚገኙትን ሉዓላዊ የኢትዮጵያ ግዛቶች ከወራሪው የሻዓቢያ ኃይል ለማስመለስ በተካሄደው ውጊያ ምን ያህል
ጓዶችህን እንዳጣህ ካንተ በላይ የሚያውቀው የለም። የፈረጠመ ክንድህን ለጠላቶችህ አሳይተሃል። ካንተ የሚጠበቅብህን ግዳጅም
በአኵሪ መንገድ ተወጥተሃል። ሆኖም፤ የጦር ሜዳ ድልህን በአልጀርስ ስምምነት ቀዝቃዛ ውኃ ተሰልችቶበት እንዳልነበረ ተደርጎ ደምህ
የከፈልክበት ሉዓላዊ ግዛታችን በፈረጠመ ክንድህ ላዛልከው ጥላት እንዲሰጥ ተወስኖበታል። ዛሬም ለአስራ ሶስት ዓመታት አንተን ዳር
ድንበር ጠብቅ ብለው በቀበሮ ጉድጓድ እንድትኖር ካደረጉ በኋላ በስመ ድርድር አሳልፈው ለኤርትራ ለመስጠት እንደራደር እያሉ የአቶ
ኢሳያስ አፈወርቂን በር በማንኳኳት ላይ ይገኛሉ። ሕገ-መንግሥቱ የጣለብህን የአገርን ዳር ድንበር የማስከበርና የኢሮብ ብሔረ-ሰብ
ለሁለት እንዳይከፈል የመከላከል ሐላፍነት አሁንም ባንተ ትከሻ ላይ የተጣለ ግዳጅ መሆኑ ለደቂቃም ቢሆን ልትዘነጋው የማትችለው
አገራዊ ጉዳይ መሆኑን በማመን በፖለቲካ ውሳኔዎች ተሳበው የሚቀርቡ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን የሚጎዱ ውሳኔዎችን እንድትቃወም
ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ለኢሮብ ብሔረ-ሰብ ተወላጆች በሞላ፤

ከኛ በላይ አከባቢያችን የሚያውቅ ሰው ሊኖር አይችልም። በአልጀርስ ስምምነትና በሄግ ውሳኔ መሠረት በርካታ የቡክናይቲ-ዓረ
መንደሮችና መላው አድጋዲ-ዓረ ለኤርትራ መከለላቸው ግልፅ ነው። ስለሆነም ባለቤቱ ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም እንዳይሆንብን
ስለተሰጠው መሬታችንና ዳር ድንበራችንን በሚመለከት ኢትዮጵያዊያንን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉና በያለንበት ማሳወቅ ይኖርብናል።

በተጨማሪም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የአገሩ ዳር ድንበር የት ድረስ እንደሆነ በግልጽ አውቆ ከኛ ከአከባቢው ነዋሪዎች ጎን በመሰለፍ
ድንበሬን አትስጡ ብሎ ለመቆም እንዲችል፣ የሄግ ውሳኔና የድንበራችን አጣብቂኝ ውስጥ መግባት፤ ከዚህም አልፎ የኢትዮጵያ
መንግሥት ባለሥልጣናት እንኳን የኛ ነው ብለው ለመጠየቅ የአከባቢውን ስም ለመጥራት መጠየፋቸውን፤ የኢሮብ መሬትና ህዝብ
ለሁለት መክፈል ማለት የብሔረ-ሰቡን ህልውና ማክተም እንደሆነ በሚገባ ተገንዝበን አንደኛ በአንድ ድምጽ እንድንቃወም፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በምታገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያዊን ሆነ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን የጉዳዩን አንገብጋቢነት እንድታስረዱ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ለኢትዮጵያ መንግሥት፤

የአንድ አገር የግዛትና የህዝብ አንድነት የማስጠበቅ ሓላፊነት የሚጣለው በሚያስተዳድራት መንግሥት ላይ መሆኑ ግልጽ ነው።አሁን
ኢትዮጵያን የሚገዛ መንግሥት ግን የአገር መከላከያ ሠራዊታችን ደም ገብሮ፤ ውድ ህወቱን በመሰዋት ወረራውን ቀልብሶ ያስመለሰውን
ሉዓላዊ ግዛታችን አልጀርስ ድረስ ተጉዞ ለተሸነፈው ወራሪ ጠላት አስረክቦ ተመልሷል። ሄግ ላይ በገላጋይ ዳኞች ፊት ቀርቦ ተገቢና
ተመዝግበው የሚገኙ የሰነድ ማስረጃዎችን ለማቅረብ ባለመቻሉ ወይም ባለመፈለጉ ሉዓላዊ ግዛታችንን ለሻዓቢያ ያስረከበው ይህ
መንግሥት ነው። የግልግል ፍርድ ቤቱ እነ ፆሮና የኢትዮጵያ ናቸው ብሎ ሲወስን የኢትዮጵያ አይደሉም ጥያቄም አላቀረብንባቸውም
ብሎ የተከራከረው ይህ መንግሥት ነው። በፍርድ ቤት ተሸንፈን እያለ አሸንፈናል ብሎ ሊያማልለን የሞከረ ይህ መንግሥት ነው።
ሻዓቢያ የተባበሩት መንግሥታት ድድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይልን በማባረር የሃያ አምስት ኪሎ ሜትር ጊዜያዊ የሰላም ቀጠና
በመቀልበስ ውሉን አፍርሶት እያለ፤ ሻዓቢያ ያፈረሰውን ውል በመንከባከብ የሄግ ውሳኔን ተቀብያለሁ ብሎ ደጋገመው በማስተጋባት ላይ
የሚገኘውም ይህ መንግስት ነው። አሁን ድግሞ ሉዓላዊ ግዛታችንን አሳልፎ ለሻዓቢያ ለመስጠት ለሽምግልና የሻዓቢያን በር
በማንኳኳት ላይ የሚገኘው ይህ መንግሥት ነው። ስለሆነ መንግስት ሀገርንና ህዝብን ወክሎ ስለ ዳር ድንብርና የሀገር ሉዓላዊነት
መደራደር በመርህ ደረጃ የሚንቀበለው ቢሆንም እስካሁን ድረስ ከህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ስለ ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ካየነው
ተመክሮ ይህ መንግስት በትክክል ዳር ድንበራችንና ሉዓላዊት ኢትዮዽያን በሚጠቅም መንገድ ይደራደርልናል ብለን ለማመን
ይቸግረናል። ስለሆነም የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛቶች በዘላቂነት ለማስከበር ፍላጎቱ ካለ፤ አሁንም ቢሆን አልመሸምና የአልጀርስን ውልና
የሄግ ውሳኔን ውድቅ ማድረጉ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለዓለም አቀፉ ማሕበረ-ሰብ በይፋ እንዲያሳውቅ እንጠይቃለን።
እኛ ኢሮቦች የራሳችንን አንሰጥም የሰውም አንፈልግም፤ ድንበራችን የት እንደሆነ ከማንም በላይ እኛ ነዋሪዎቹ እናውቀዋለን፣
ከኢትዮጵያ መንግስትና ከሻዕቢያ ጣልቃ ገብንት ነጻ ከሆን በድንበር ከሚዋሰኑን ኤርትራዊያን ወንድሞቻችን ጋር ዳር ድንበሩን
ያለምንም ችግር እኛው ራሳችን በድንበሩ አከባቢ የምንኖር ህዝቦች የየራሳችንን ቦታ በግልጽ ስለምናውቅ ያለምንም ችግር ተወያይተን
ለመፍታት እንችላለን። እኛ የነሱን እንደማንፈልግ እነሱ ያውቃሉ። እኛም እነሱ የኛን ይፈልጋሉ ብለን አንገምትም። ተጠቃልሎ
ሲመነዘር የድንበር ማካለል ጉዳይ፣ ለሁለቱ ህዝቦች መተው ያለበት ጉዳይ ነው። ከዛ ውጭ አሁን በሚታየው መልኩ ከቀጠለ ለሁለቱ
አገዛዞች ጊዜያዊ ፖለቲካ ጠቀሜታ ሊኖረው ይችል እንደሆነ እንጂ፤ ዘላቂ መፍትሔና የተረጋጋ ሰላም ለአከባቢውም ሆነ ለሁለቱ አገሮች
ለማምጣት ፈጽሞ አይችልም!
ከኢ.መ.ተ.ማ
ታሕሣሥ 2005 ዓ.ም

posted by Aseged Tamene at
« Last Edit: September 12, 2016, 12:18:06 PM by staff3 »