Author Topic: "ወሸኔ" ፤ መፈንቅለ-መንግሥት ! ድንቄም ኹዴታ' !  (Read 1410 times)

staff3

  • Global Moderator
  • Newbie
  • *****
  • Posts: 260
ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ
Finote Democracy Voice of Ethiopian Unity
efdpu@aol.com  www.Finote.org
 
በፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ራዲዮ
በሐምሌ 17 ቀን 2011 ዓም የተላለፈ ሐተታ

"ወሸኔ" ፤ መፈንቅለ-መንግሥት ! ድንቄም ኹዴታ' !

ኩዴታ' የሚለው ቃል ከፈረንጅ ቋንቋ ከፈረንሳይ -- የተኮረጀ ነው። ትርጉሙ ደግሞ ፤ በድንገት፤ ፈጣን ለውጥ አካሂዶ፤ በአስቸኳይና ባልታሰበ ድንገተኛ ርምጃ ፤ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በኃይል መቀየር ማለት ነው። በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት፤ ሳይሰማና ሳያይ፤ ሳይጠረጥርና ሳይነቃ፤ አደጋ ጥሎ ማስወገድና በምትኩ ሌላ ቡድን ሥልጣን የሚይዝበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሆነ ይታወቃል ። ያ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፤በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት፤ የመረጃ ተቋም ፤ ማነኛውንም ፀረ- መንግሥት እንቅስቃሴ ሁሉ እንዳላየ አድርጎ ያልፋል ማለት አይቻልምና ኩዴታ የሚያስቡ ሁሉ ፤ከመንግግሥት መረጃ ክትትል ፤ በርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል ። ቢቻል ደግሞ፤ በኩዴታው የሚስማማና ታማኝነቱም የተረጋገጠ ከሆነ፤ የመንግሥት መረጃ ሰው / ሰላይ የሴራው ተካፋይ እንዲሆን ማድረግን ያስፈልጋል ። የመረጃውን ክፍተት ሊሸፍን ይችላልና እርሱን መጠቀም አይከፋም። ያ ከሆነ፤ የስለላ ሰው የሚያከናውነው ተግባር በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ኩዴታ፤ ከጥንስሡ እስከ ሂደቱና አፈጻጸሙ ድረስ፤ በምሥጢር ተይዞ ፤ ጉዳዩን በሚያከናውኑት ጥቂት ሰዎች ብቻ ተወስኖ የሚፈፀም ነው ። ኩዴታውን የሚያከናውኑት ሰዎች እጅግ ሲበዛ፤ እርስ በእርስ የሚተማመኑ፤ የሚግባቡና ያለ ማቋረጥ፤ ለብዙ ጊዜ የሚተዋወቁ ሊሆኑ ይገባል ። የዐላማ አንድነትና ፅናት ኖሯቸው፤ ቆራጥነትን ፤ድፍረትንና ወሳኝነትን አንግበው የሚነሱ ሰዎች ሆነው መገኘት አለባቸው። ዕቅዳቸውን ለማሳካት የሚያስችሏቸውን ዐበይት ነገሮች ሁሉ በዕቅዳቸው ውስጥ አስገብተው ከ ሀ እስከ ፐ ድረስ ያለውን ዕቅድ ሁሉ ፤ በዝርዝር ተወያይተው ሙሉ ስምነት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል ። ሁሉም የተስማሙበትን ዕቅድ፤ ሁሉም ያለ ሃኬትና ማመንታት መፈፀም አለባቸው። ቃል -ኪዳን ተገባብተው የጀመሩትን ዕቅድ ከፍፃሜ ማድረስ፤ ተግተው መስራት ይጠበቅባቸዋል። ኩዴታው ተሳክቶ የታቀደለትን ግብ እንዲመታ ማደረግ የጠጠሳሾቹ ቀዳማይና ደሃራይ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል። አንድ ጊዜ በቅዱ አምነው ከገቡበት በኋላ፤ ወለም ዘለም፤ ማቄን ጨርቄን የለም ! ፈጥነው ማከናወን አለባቸው።

ድርጊቱ የሚከናውንበት ቦታ፤ ጊዜ፤ ዒላማና ሌሎች ያልታሰቡ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ሊከሰቱ የሚችሉበት ዕሳቤ ሁሉ እግምት ወስጥ መግባት ይኖርባቸዋል ። ዝርክርክነትና ግዴለሽነት ፤ ለኩዴታ መክሸፍ ምክንያቶች ይሆናሉ። በተራራቀ ቦታና በተለያየ የጊዜ ቀመር፤ ኩዴታን ማከናወን ቀርቶ ማሰብም እንኳን ጅልነት ነው። በራስ ላይ የሰላ ሰይፍ አስቀምጦ እንደ መሄድ ይቆጠራልና ጨርሶ ማስብ አይገባም ። በግንቦት 81 ዓም አዲስ አበባና አሥመራ ባለ እርቀት ለማቀዳጀት የተደረገው ሙከራ፤ የስንት ዜጎችን ህይወት አንዳጠፋ የቅርብ ትዝታ ሆኖ አልፏል። የዚያን ጨካኝ አገዛዝ ዕድሜም እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል ።፡ ኩዴታን ለማከናወን ችሎታ ያለው ባለሙያ / መሆንን ይጠይቃል። የሙያ ጥረት / የሚጠናወታቸውን ሰዎች / ማስገባት ቀርቶ፤ በአካባቢው እንዲገኙ ማድረግ/ ወድቀትን ከመጀመሪያው መጋበዝ ነው ።

በኩዴታ ዕቅዱ ወስጥ፤ የማነኛውንም ዜጋ ህይወት በከንቱ እንዳይጠፋ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ የኩዴታው ጠንሳሾች በሚገባ ሊያስቡበትና ሊጨነቁበት ግድ ይላል ። ኩዴታው የሚከናወንበት ስዐት ከመንፈቀ- ሌሊት እስከ ንጋት ባለው ጊዜ ቢሆን ይመረጣል ። ይኽም ማለት፤ ከሌሊቱ ስድስት/ ፮ ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ( እንደ ኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ማለት ነው) ባለው ጊዜ ቢሆን ይመረጣል ። የዚኽ ጊዜ ወቅት የሚመረጥበት ምክንያት ፤ አብዛኛው ነዋሪ በቤቱ ትከትቶ ስለሚገኝ፤ ሁከትና ግርግር እንዳይፈጠር ከማስብም በላይ ፤ የዜጎችንም ደኅንነትና ህይወት ከአደጋ ለመጠበቅ ዕሳቤ ጭምር ነው።

በሀገራችን፤ ከ 1916 ዓም ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ የተለያዩ የመፈንቅለ- መንግግሥት ሙከራዎች ተድርገዋል። አንዳቸውም አልተሳኩም። እስካሁን የተሞከሩት የመፈንቅለ - መንግሥት ሙከራዎች ሁሉ ለምን እነደከሽፉ የተለያዩ መክንያቶች ቢነገሩም፤ ዋናው ግን ከኅደትና አንዱ ሌላውን አጋልጦ የመስጠት አባዜ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል ። በሀገራችን ያልተሳኩት ኩዴታዎች በምን ምክንያት እንደከሸፉ የመዘርዘሩ ተግባር ፤ የታሪክ ተመራማሪዎች ድርሻ እንደሚሆን ብንረዳም፤ ትርክት- ቀመስም ይሁን፤ በሌላም መንገድ የሚታወቁትን ለዐብነት ጥቂቶቹን መጥቀሱ አይከፋም ።

 በ1916 ዓም በአልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን ላይ የተጠነሰሰው መፈንቀለ -ሥልጣን፤ ምሥጢሩ በከሃዲዎች በመገለጡ ምክንያት በወቅቱ የአራዳ ዘበኛ አለቃ በነበሩት ባላምባራስ አበበ አረጋይ ( የኋላው ራስ አበባ አረጋይ) እንደከሸፈ በአፍ-ታሪክ እየተጠቀሰ ቆይቷል ።
 በ1943 ዓም በነ ቢትወደድ ነጋሽ በዛብህ፤ አለቃ ፈጠነ፤ መቶ አለቃ በቀለ አናሲሞስና ሌሎች ለውጥ ፈላጊዎች ንጉሱን ለመገልበጥ ሞክረው ፤ ምሥጢራቸው ፤ በጥቂት የዓድማው ተካፋይ በነበሩ ጥቂት ከሃዲዎች ተጋልጦ ከሽፏል ይባላል።

 የ1953ቱ መፈቅለ- መንግሥትን ሙከራ የንጉሱ ክብር ዘበኛ መኮንኖች ሞክረውት ከሽፎ ቀርቷል ።
 በ1954 ዓም በነ ፊታውራሪ ኃይሉ ክብረት ሙከራ ተድርጎ ከሽፏል ።
 በ1957 ዓም በነኮሎኔል ዕምሩ ወንዴ፤ በነ ኮሎኔል አስናቀ ዕንግዳና በነ ኮሎኔል አሰፋው ዳርጌ ተሞክሮ በከዲዎች ምስጢር አጋላጭነት ከሽፏል ።
 በ1965 በዐርበኛው ደጃዝማች ታከለ ወልደ ሐዋርያት መሪነት ንጉሱን ከሥልጣን ለማውረድ የተጠነሰሰው ሴራ፤ በከሃዲዎች ተደርሶበት፤ ታከለ ወልደ ሐዋርያት እጅ አልስጥም ብለው፤ እራሳቸው በመሰዋት፤ የጀግና ኅልፈት ፈጽመዋል። ከሀዲዎቹም በንጉሱ የአውራጃ ገዥነት ተሹመዋል ተብሏል ።
3
 1981 ዓም ግንቦት ወር በደርግ ውስጥ የተሞከረው እንደዚሁ ስይሳካለት ቀርቷል።

ከላይ የተጠቀሱትን ሰባት የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራዎች የመዝግብናቸው፤ እንዲያው ለግንዛቤ ያኽል እንጅ ፤ ሌሎች በርካታ ኩዴታዎች እንደነበሩ በየጊዜው ተጠቅሰዋል። ለምን አልተሳኩም? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ መላ-ምቶች ሊደረደሩ ቢችሉም፤ ሁሉም ሊስማማበት የሚችለው ግን ፤ ያለመተማመንና የእርስ በርስ መከዳዳት እንደሚሆን ሕዝቡ ይገነዘበዋል። ይኽ አሳፋሪና መጥፎ ባኅል ፤ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑ ንጹህ ኅሊና ላለው ዜጋ ሁሉ ልቡን ይሰብረዋል።
ዛሬ፤ በዚኽ ርዐስ ላይ መጠነኛ ግንዛቤ ለመስጠት የተፈለገበት ምክንያት ግን ፤ የዐብይ አህመድ አሊ ቡድን ሰሞኑን ባኅርዳርና አዲስ አበባ ከተሞች የተፈፀሙትን ግድያዎች አስመልክቶ ፤ "መንግሥቴን ለመገለብጥ ኩዴታ ' ተሞክሮ አከሸፍኩት " የሚል ፕሮፓጋንዳ በመሰማቱ ነው ። " ላም ባልዋለበት ኩበት መልቀም " የሚቻል ከሆነ፤ ይኽ ፕሮፓጋንዳ ሊያስኬድ ይችል ይሆናል ። ግን ደግሞ ፤ ሁሉም እንደሚረዳው ፤ በሁለቱ ከተሞች የተፈፀሙት ሁኔታዎች ፤ የኩዴታ ባህርይም ሆነ ተግባራት የላቸውም። ተራ የነፍስ ግድያ ወንጀሎች ናቸው። በአብይ ዐህመድ ባለሥልጣናት ተሳትፎ የተፈጸሙ የእርስ-በርስ ነፍስ መጠፋፋት የተራ ግድያ ወንጀሎች ነበሩ ብሎ ማለፉ ይመረጣል ።
በላይኛው አንቀፅ የተዘረዘሩትን የመፈንቅለ መንግሥት ( ኩዴታ') ባኅርይ፤ ዐላማና ግብ፤እንዲሁም፤ ከመነሻና መድረሻቸው ጋር የሚተዋወቅ አይደለም ። እንዲሁም የኩዴታን መስፈርቶች ማሟላት ይቅርና፤ ከኩዴታ ምንነት ጋር እንኳ የሚተዋወቅ አይመስልም።

የእርስ በርስ ግድያ፤ እንደ መፈንቀለ መንግሥት የሚቆጠር ከሆነ፤ ደርግ በበኩሉ፤ በ17 ዐመት ቆይታው ፤እርስ በእርስ ሲጠፋፋ፤ ሲገዳደልና ሲፋጅ ኖሯል። በባህር-ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች የተካሄዱት ግድያዎች ፤ ከእርስ በእርስ መጠፋት የዘለለ ተግባር አላሳዩም። ሙከራውም ፤ ለለውጥ ሳይሆን፤ በመካከላቸው በተፈጠረው ጠብና የሥልጣን መራኮት ምክንያት የተካሄደ የርስ በእርስ መገዳደል እና ብሎም፤ የአማራውን ክፍል ለማጥቃት እንጂ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ነበር ለማለት ፈጽሞ አይቻልም።

ተመክሮዎች እንደሚያስረዱት፤ ምንጊዜም ቢሆን፤ ማነኛውም ኩዴታ ከመካሂዱ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ፤ የሚከተሉቱ ተግባራትና ሁኔታዎች ፤ በጥብቅ ቁጥጥር ስር ሊሟሉ ይገባል ።

 1ኛ. ስትራትጃዊ የተባሉት ቦታዎች ሁሉ በቁጥጥር ስር መዋል አለባቸው። ለምሳሌ፦---
ራዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች፤ መገናኛ፤ መጓጓዣ ማዕከላት፤ ባንኮች፤ ሆስፒታሎች፤ እስር ቤቶችና አይሮፕላን ማረፊያዎች ወደቦች ፤ የመብራት ኃይል መስጫና የውሃ ማከፋፋያ ቦታዎች አግልግሎቶቻቸውን እንዳያቋርጡ ይደረጋል።

2ኛ. ቢያንስ፤ አንድ የታጠቀና የቆረጠ ሠራዊት በኩዴታ አድራጊዎች ዕዝና ቁጥጥር ስር መሆን ይገባዋል።፤ ተልዕኮውም፤ ኩዴታውን መከላከልንና ተጻራሪ ኃይልም ካለ ያንን ማጥቃት ይሆናል። ሁኔታውን ለማረጋጋትና ለማስከን ይታዘዛል።

3ኛ. የሀገሪቱ መከላካያ ሠራዊት ፤ በአንደኛ ደረጃ በተጠንቀቅ ዕዝ እንዲሆን ይደረጋል። ይኽም፤ የውጭ ኃይል ሁኔታውን ተጠቅሞ የሀገሪቱን ግዛታዊ አንድነትና ሉዓላዊነት እንዳይደፈር ለመቆጣጠር ነው ።
እንግዲኽ፤ ከአንድ እስከ ሦስት ተራ ቁጥሮች የተዘረዘሩት መሠረታዊና ስትረተጂያዊ ተግባራት በቅድመ ዝግጅት ሳይከናወኑ ፤ በምን ምትኀት ነው፤ ኩዴታ አደረጉ የተባሉት ግለ-ሰቦች መፈንቅለ-መንግሥት ሊያከናውኑ የሚችሉት? መጀመሪያ ሳይደረግ እንዴት ከሸፈ ይባላል? የዐብይ አህመድ ምናባዊ አስተሳስብና የጋሻ-ጃግሬዎቹ ሥነ-ልቦና መቅበዝበዝ የፈጠረው መፈንቅለ መንግሥት ብዥታ መሆኑ ግልጽ ነው ።

በብዙዎች ግምት፤ ሁኔታውን ተጠቅሞ፤ የኮሎኔል ዐብይ አህመድ አገዛዝ የማይፈልጋቸውን ወገኖች ፤ በተለይም፤ የዐማራ ተዎላጆችን ቅስም ለመስበርና የመሪዎቻቸውንም ሞራል ለማድቀቅ የታለመ ዕኩይ ተግባር እንደሆነ አድርገው ወስደውታል። ለዚኽ አባባል እንደማጠየቂያ ሊወሰድ የሚችለው፤፤ ሁኔታውን ተከትለው አንዳንድ የውጭ ሀገር ሰዎች ፤ ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚረጩት መርዛማ ተንኮል ነው። በተለይም ሄርማን ኮኾን የተሰኘ ያንድ ባዕድ አገር ዜጋ፤ የነዛውን ፀረ-ዐማራ ስብከት፤ ሁሉንም ዜጋ አስቆጥቶታል። በወገኖቹ ላይ የሚነዛውን የጥላቻና የርስ በርስ ፍጅት ቅስቀሳ ፤ ለዚች ሐተታ ምክንያት መነሻ ሊሆን ችሏል።

በኢትዮጵያውያን ላይ ላይ ያነጣጠረውን ተደጋጋሚ መርዛማ ፕሮፓጋንዳና የጥፋት ዘመቻ ሰምቶ በዝምታ ለማለፍ አይቻልም። የውጭ የጥፋት ኃይሎች አደብ ሊገዙ ይገባቸዋል፡፡ኢትዮጵያዊው ሁሉ፤ አቅሙ የሚፈቅድለት መከላከል ያደርጋል። ሄርማን ኮኼንና ሌሎችም ባዕዳን ፤ በኢትዮጵያ ላይ የሚያካሂዱት ያልተቋረጠ የርስ በርስ ዕልቂት ዘመቻ አያስገርመንም። በነርሱም ልንፈርድ አይገባንም። ። ምክንያቱም ከጠላት መርዝን እንጅ ማርና ወተትን አንጠብቅምና ! ጥፋቱ የኛው፤ የኢትዮጵያውያኑ ነው ። ራሳችንን አስንቀናል። አዋርደናል። መተባበር ባለማቻላችን አቅማችንን አሳንሰናል። በጠላቶቻችን ዘንድ ተንቀናል። " ባለቤቱን ካልናቁ፤ አጥሩን አይነቀንቁ ! " ተብለን ተሹፎብናል! ታላቅ ሀገር እያለን ፤ ራስችንን ዝቅ አድርገን ፤ ሀገራችንንም አሳንሰናል! በታሪክ የተከበረች ሀገር እያላችን ፤ እኛ ግን እርሷን አላከበርናትም። ሰድብን ለሰዳቢ፤ አዋርደን ለአዋራጅ ዳርገናታል! ሕዝቡን ያላከበረ አገዛዝ ያላት ሀገራችን፤ ዐለም ያከብራታል ብለን መጠበቅ የለብንም ። እነ ኮሎኔል ዐብይ አህመድ፤ በሥልጣን ሽኩቻ፤ እየተገዳደሉ መፈንቅለ -መንግሥት " ኩዴታ ተጠንስሶብን አከሸፍነው ! " የሚል ተውኔት ያሳያሉ። ይኽ ደግሞ ወሃ የሚቋጥር አይደለም።

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ፤ ዘረኛ የሆኑ ግለሰቦች የሚጫወቱባ ሀገር ሆናለች ።

ተደጋግሞ ተደጋግሞ እየተነገረ ያለው፤ ኢትዮጵያ ፤ በርዥም ታሪኳ አጋጥሟት የማያውቅ ችግር ላይ ወድቃለች! ይኸውም፦

 1ኛ. በዘር ጥላቻ መርዝ ተበክላለች። ቋንቋንና ዘርን ማህከል ያደረገ አገዛዝ ወድቆባታል።
2ኛ. በሀገራዊ መንግሥት አትወከልም። ወደ መሳፍንት አገዛዝ በማምራት ላይ ነች ብለው የሚሰጉ አሉ። የህግ የበላይነትና ፍትኅ-ርትዕ እየቀረ የጅምላ ፍርድና በአደባባይ የመንጋ ብያኔ ተተክተዋል። " እኛ ኢትዮጵያውያን መባባሉ እየቀረ እነርሱና እነዚያ በሚል የክፍፍል ቋንቋ ተመርዛለች።
3ኛ. ሀገራዊ አንድነትን የሚያስከብርና ከውጭ ወራሪ የሚከላከል ፤ ኢትዮጵያዊ ጦር ሠራዊት አላት ብሎ ማለት ያስቸግራል።

4ኛ. ተተኪውን ኢትዮጵያዊ ትውልድ ማዘጋጀት አልተቻላም ። የባዕዳን ርካሽ ባኅሎች፤ አሳፋሪና መርዘኛ ድርጊቶች ወጣቱን ትውልድ እየበከሉት ይገኛሉ ። ሥነ ምግባር፤ እየጠፋ፤ ራስ ወዳድነት እየተተካ በመሄድ ላይ ነው። መተሳሰብና መተዛዘን እየቀረ፤ ስርቆትና ግድያ፤ ሸፍጥና መከዳዳት ፤ ዝርፍያና ቅሚያ በቦታው ተተክተዋል። መርኅ ( ፕሪንስፕል) የሚባለው ቋንቋ፤ ከመዝገበ ቃላት ከወጣ ቆይቷል።

5ኛ. ልመና፤ የጎዳና ተዳዳሪነት ፤ ስራ ዕጦት፤ ቦዘኔነትና ዋልጌነት በህዝብ ላይ ተጭነው ፤ሰፍነው ይገኛሉ ።
ታዲያ ምን እናድርግ ብለን መጠየቅ የዘዋትር ተግባራችን መሆን አለበት ! መጀመሪያ----- ፡

ሀ. ጠላቶቻን ካሰናዱልን የጥፋት ወጥመድ እንዳንገባላቸው አንድነታችንን አጠንክረን ፤ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ድርጃ መድረስ አለብን!

ለ. ከእርስ በርስ መከፋፈል የምንድነው፤ የጠላት ፕሮፓጋንዳ ሰላባ ሳንሆን ስንቀር ብቻ ነው። ለጠላቶቻችን መመቸት የለብንም።

ሐ. ለዴሞክራሲ ሥርዓት መምጣት ትግላችንን ማስተባበር አለብን። ያለዴሞክራሲ ሥርዓት ምንም መልካም ወጤት አይመዘገብም።የሕዝብ የሽግግር መንግሥት ፍ ፍላጎት የከበርለት ፤ ይስከብር በትግሉ!

መ. በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ፤ ተባብሮ እንዲነሳ እንድትነሳ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን !!!!
ሠ. ኩዴታም ሆነ ጥገናዊ ለውጥ ለሀገራችን ዘላቂ መፍተሄን አያመጡም!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር !