Author Topic: መንግሥትን ማመን፤ መርጦና ተጠንቀቆ ነው !  (Read 1535 times)

staff3

  • Global Moderator
  • Newbie
  • *****
  • Posts: 260
ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ
Finote Democracy Voice of Ethiopian Unity
efdpu@aol.com   www.Finote.org

በፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ራዲዮ
በ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓም የተላለፈ ሐተታ

መንግሥትን ማመን፤ መርጦና ተጠንቀቆ ነው !

መንግሥት የተሰኘው ተቋም ሊታመን የሚችለው ፤ ሕዝቡ እራሱ ፈቅዶ በመሰረተው ሕግ መንግሥት አማካኝነት የመረጣቸውን መሪዎች መቆጣጠር ሲችል ብቻ ነው። በሌላ አገላለጽ፤ በሁለቱ መካከል መተማመን የሚገኘው ፤ ሕዝብ በፈቃዱ ራሱ ባዘጋጀው ህገመንግሥት መሠረት፤ የመረጠውን መንግሥት ፤ ራሱ ከሥልጣን የማውረድ ኃይል ሲኖረው ብቻ ነው። ይኽ መሠረታዊ ሀቅ በታሪካችን ዕውን ሆኖ አያውቅም ። ባለመሆኑም፤ የሀገራችን የፖለቲካ ሥር ዓት፤ እስከዛሬ ድረስ ፤ጥርጣሬን እንጅ ፤ መተማመንን፤ ሁከትን እንጅ፤ መረጋጋትን ሊያሰፍን የሚችል ሳይሆን ቆይቷል። ጭቆናን፤ እስራትን ፤ ግድያን፤ ማሳደድንና ከህደትን ሁሉ የሚፈፅመው መንግሥት የተባለው ተቋም ነው። ለዚኽ ሀቅ እንደ ማስረጃ የሚጠቀሰው ኢትዮጵያን ከድቶ የኮበለለው የደርግ መንግሥት ነበር ። መንግሥት የተሰኘው ተቋምና ሕዝብ በመካከላቸው ዕምነት የሚባል ነገር ሰፍኖ አያውቅም ። በመሆኑም፤ "መንግሥትን ማመን ቀብሮ ነው !" ብሎ ቢያማርር ፤ ሕዝብ አይፈረድበትም! አሁንማ ፤ ሕዝብና መንግሥት ብቻ ሳይሆኑ ፤ ሕዝብ ለሕዝብ እንኳን መተማመኑ እየተሟጠጠ ነው ። የዚህ ምክንያቱ ፤ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ፤ ሀገሪቱን በመቆጣጠራቸው እንደሆነ አይካድም። ኢትዮጵያዊነትንና በጎሣ ላይ የተመሠረተን ፖለቲካ አጣጥሞ የሚመራ ኃይል በመጥፋቱ ፤ የዜጎቿን መበጣበጥ ለሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች የረዥም ጊዜ ኅልማቸው ዕውን ሆኖላቸዋል። የሰሞኑ ግድያ መንሰዔው ሕዝብን ማዕከል ያላደረገ ብቻ ሳይሆን ፤ ከናካቴውም፤ ሕዝብን ሙሉ በሙሉ ያገለለ መሆኑም ጭምር ነው።

ዛሬ በሀገራችን ፤መተማመን በጥርጣሬ ተተክቷል ። ሕዝብ ለሕዝብ መተማመን እየቀነሰ ሁሉም ለጎሳውና ለጎጡ ማሰቡን ሥራየ ጉዳየ ብሎ ተያይዞታል። በዜጎች መክከል መተመማን በመጥፋቱ ምክንያት ፤ የጋራ ጠላት የሆነባቸውን ጨቋኝ መንግሥት፤ በጋራ ሊያስወግዱ አይችሉም። ምናልባት በየፊናቸው አመፅ አካሂደው መንግሥትን ማዳከም ቢሳካላቸውም እንኳን፤ ዜጎቹ ሊስማሙ ባለመቻላቸው ምክንያት፤ የሚስማማቸውን መንግሥት በጋራ ሊመሰርቱ አልቻሉም ። ይኽ አባባል፤ በዘፈቀደ የሚነገር ሳይሆን፤ ለአለፉት አምሳ ስምንት ዐመታት በተደጋጋሚ የተከሰተ ሀቅ ነው ። የአምሳ ስምንት ዐመታት የሀገሪቱ ፖለቲካ ሂደት ይህንኑ ያረጋግጣል። ካለፈው ስህተት መማር አልተቻለም። ይህ ደግሞ ፤ ባለፈ ታሪክ እስረኞች ሆነን እንድንቀጥል ምክንያት ሆኖብናል። ያለፈ ታሪክ እስረኛ መሆን ደግሞ ለመፃኢ ዕድላችን የሚስማማ ራዕይ እንዳናይ አድርጎናል። ያለፈው የጨለማ ጊዜ፤ የመጭውን ብሩህ ተስፋ እንዳናይ አጨልሞብናል።

በተከታታይ ሦስቱን ሥርዓቶች በትግሉ ያስወገደ ሕዝብ ፤ የሚስማማውን መንግሥት በጋራ ለመመስረት አልተሳካለትም ። ተስማምቶ ማፍረስ እንጅ ተባብሮ መገንባትን አላወቀበትም። በፍርሻው ላይ በሚፈጠረው ግርግር፤
አጋጣሚውን ተጠቀመው ፤የመንግሥት ሥልጣን በሚነጥቁ አምባገነኖች ፤ ሀገሪቱና ነዋሪዎቿ ሰለባዎች ሆነው ቀርተዋል። ለዚኽ ሁሉ ችግር፤ እንደ ዐይነተኛ ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው፤የሀገርን ዘላቂ ጥቅም ከግል የፖለቲካ ድርጅት ጥቅም በላይ አሻግሮ ያለማየት ችግር ሆኗል። ለጊዚያዊ ሥልጣን ማርኪያ መሽቀዳደም እንጅ ፤ ለሀገርና ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም የሚሰራ ቀርቶ የሚያስብ እንኳ አልተገኘም። በሹሙ የፖለቲካ ምኅዳር ሥልጣን እናገኝ ይሆናል ብለው የተኮለኮሉት ሁሉ ፤ ሰሞኑን በተፈጠረው ሁኔታ ፤ እንደተተኮሰበት ድኩላ ግራ ተጋብተው ደንዝዘዋል። ቆይተው" ያመኑት ፈረስ ጣል በደንደስ " የሚል የታሪክ ጠባሳን ሸፍነው ይኖራሉ ። እስከኖሩ ድረስ ! የሀገሪቱ ችግር መሠረታዊው ምክንያት ምን እንደሆነ ግራ የገባቸው አንዳንድ ተመልካቾች፤ " መንግሥት ይቀየርልን ! " የሚሉትን መፈክር፤ " ሕዝብ "ይቀየርልን ! ወደሚለው መፈክር እንደለወጡት ይነገራል። " የቸገረው ገበሬ ለዘር ያስቀመጠውን ጥሬ ቆልቶ ይበላል " እንደተባለው ሆነና ፤ ይኽን ቢሉ አይፈረድባቸውም ።

ይግረማችሁ ተብሎ፤ በአጋጣሚ ሥልጣን ጉጉት ምክንያት ፤ የነበሩበትን ድርጅት ማፍረስ እንደ አዲስ ፈሊጥ ተይዟል። የሥልጣን ጉጉት ሀፍረትንና ይሉኝታን ስለሚያጠፋ፤ ዐይነ ኅሊናውን ይጋርድበታል። ይኽንን የሕዝብ ትዝብት ደግሞ፤ ማንም አፈ-ጮሌ ሊቋቋመው አይችልም። መንግሥት በፈረሰ ቁጥር ፤ ተሽቀዳድሞ ሥልጣን ለመያዝ ማቋመጥ እንጅ ፤ ከሕዝቡና ከሀገሪቱ ዘላቂ ጥቅም አኳያ የሚሆነውን ትልም ለመንደፍ የሚያበቃ ዝግጅት፤ ዕውቀትና ፍላጎት አልነበረም። አሁንም ያው ሆኗል ።

የሚለዋወጡት ገዥዎች ሁሉ፤ የስምና የቅርፅ ለውጥ ካልሆነ በስተቀር፤ የይዘት ልዩነት የሚያመጡ አልሆኑም። በበጎ ፈቃድ ብቻ ለሀገር የሚጠቅም ሥራ የሚሰራ መንግሥት ይገኛል ብሎ መመኘት ፤ ሕዝብ ሳይርመጠው የሚመጣን መንግሥት ማንነት ካለመረዳት የሚመጣ አስተሳሰብ ነው። የሀገር መሪነት ሥልጣን የሚመነጨው ከሕዝብ መሆኑን ያለመረዳት ችግር አሁንም በሀገሪቱ የፖለቲካ አድማስ ላይ ሰፍኗል። ካለፈው የተሻለ ሳይሆን አይቀርም በሚል ቀቢፀ ተስፋ ውስጥ መግባት፤ እጅና እግርን አስሮ በመቀመጥ፤ አመፅን ማዳፈን ይሆናል ። ሕዝብ ራሱ በራሱ የራሱን አመፅ ማዳፈን ማለት፤ አምባገነኖችና አስመሳይ የፖለቲካ ተዋናዮች የሀገሪቱን ዕድል በዘፈቀደ እንዲፈነጩበት መፍቀድ ማለት ነው።

ዛሬ ሀገራችንን የቁም ስቃይ እያሳያት ያለው ቀንደኛው ምክንያት፤ የኢሕአዴግ ጎሳን መሰረት ያደረገው ፌዴራል መዋቅር ነው ። የብሄር ተዋናይ ሁሉ እንደ አሻው መፈንጨቱን ስለቀጠለ ነው። የአካባቢ መንግሥታትና ብሄራዊ መንግሥት ነኝ ብሎ አዲስ አበባ የተሰየመው ቡድን በዐላማና ግብ አይለያዩም ለማለት ቢይስችልም፤ የኃይልን ሚዛን አስመልክቶ ግን ፤ ያልተመጣጠን በመሆኑ፤አንዱ ከሌላኛው ጋር ዐይንህ ለአፍር በመባባል ላይ መሆናቸው ነው። ከዚኽ አልፈው -ተርፈው፤ በመጠፋፋት ደረጃ በመድረሳቸውም ጭምር ነው ። ሌላው ይቅርና እራሳቸው በአንድ ላይ የጻፉትን ሕገመንግሥት እንኳ ሊያከብሩት አልቻሉም። የሥልጣን እርከንም ሆነ የመዋቅር ጠገግ በተቃርኖ የተወሳሰበና የተመሰቃቀለ በመሆኑ ፤ ኢትዮጵያ፤ ሀገረ- መንግሥት የሆነች ሀገር ናት ማለት አይችልም።

አዲስ የሚመጣው ፤ ማንነቱና ምንነቱ በማያጠራጥር መልኩ በውል ሳይታወቅ ፤ ከሰማየ- ሰማያት የገዘፈ እልልታ ማሰማት፤ አዲስ መጭውን በቀቢፀ-ተስፋ እንዲማልል ከማድረግ የተለየ ትርፍ አያመጣም። በጥገናዊ ለውጥ ላይ ለማተኮር 3
ግን ግብዐት ይሰጠዋል። ይህችን ስጦታም ለሥልጣኑ እንዲያመቸው እያጣጣመ ይጠቀ ምበታል ። አሁን ዐብይ አህመድ የሚፈፅመው ይኽንኑ ነው። ዛሬም እንደ ትላንቱ፤ ሕዝብና መንግሥት ተማምነው የሚኖሩበት ድባብ የለም። ይልቁንም ፤ በዐይነ- ቁራኛ እየተያዩ፤ አንዱ ሌላውን የሚያጠፋብትን ሴራ በማውጠንጠን ላይ ይገኛሉ።

የውቅቱ ሁኔታ ሊያስረዳ የሞከረው፤ ከእንግዲኽ ወዲያ፤ አንዱ ሌላውን እያታለለ የሚቀጥልበት መንገድ እየተዘጋ መሄዱን ነው። ሹሙና ተባባሪዎቹ ሰሞኑን የፈጸሙት ሴራ ፤ ሥልጣናቸውን ከአደጋ ለማዳን የተጠቀሙበት ድርጊት ቢሆኑም፤ አጋጣሚውን ተጠቅመው፤ የዐማራውን ኅብረተሰብ፤ እየተከታተሉ ለመጥፋት የማጠየቂያ ድልዳል ሆኗቸዋል። ዱሮውንም ቢሆን ተጨንቀውበት ስለአልነበር፤ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥቅምና ፍላጎት ማዕከል ባደረገ ተግባር ላይ ይሰማራሉ የሚል ሰው የለም። መፈንቅለ- መንግሥት ( ኮዴታ ) አከሸፍን ብለው በማታለል ፤ የማወናበጃ ዘዴን ተጠቅመው፤ በሥልጣን ማጠናከሪያና ማቆያ ሂደት ላይ ርብርቦሹን ይቀጥልበታል። የሹሙን ሰብዕናም እርቃኑን በማስቀረት፤ ማን መሆኑን መስክሯል። የኖቭል የሠላም ሽልማት ይገባዋል ሲሉ የነበሩ ሁሉ ፤ አንገታቸውን ደፍተዋል።

ሰሞኑን በተፈጠረው ተንኮል ምክንያት፤ የብዙ ቤተሰብ ኑሮ እንዳልሆነ ሆኗል። ያያሌ ንፁህ ሕይወት ተቀጥፏል ። የሹሞቹ አስተዳደር፤ የሚጠረጥራቸውን ዜጎች ሁሉ እያሳደደ ማጥፋቱን ቀጥሎበታል ። የዜጎቹም ተስፋ ፤ለወደፊቱ ዕድል ብርሃን ፈንጣቂ መሆኑ እያቀረ፤ ሁሉም የገዛ ህይወቱን ባጭሩ የሚቀጭበትን መንገድ ምርጫው ለማድረግ ተገድዷል። እንደ በሬ እየተጎተተ ወደ ማረጃው ቄራ ከመሄድ ይልቅ፤ እራሱን እየተከላከለ መሰውር ያለዚያም ፤ አጥፍቶ መጥፋትን ከመምረጥ ውሳኔ ላይ ይደርሳል ። የዚኽ ሁሉ ጠቅላላ ድምር ፤ ሀገሪቱን ለኪሳራ መዳረግ ነው ። እርስ በእርስ መጠፋፋትና መፋጀትን ያመጣው በሥልጣን ላይ ያለው ብሄረተኛ ቡድን ነው። ሕዝብ ሙሉ ተሳትፎ እንዳይኖረው የሚደረግ የፖለቲካ ስልት ያመጣው ሰበብ ነው ። ፤ ዜጎቹን የበይ- ተመልካች እያደረገ ፤ መሪዎቹን ግን እርስ በርሳቸው እንደውሻ ያናክሳቸዋል ።

አምባገነኖች የሚገዙት ሀገር፤ በጭንቀት ድባብ ሲወጠር ፤ ገዥዎች ውጥረቱን ለማስተንፈስ የሚጠቀሙበት ብልሃት፤ አስደንጋጭ ሁኔታ የተፈጠረ በማስመስል፤ የሕዝቡን አቅጣጫ ሊያስለውጥ የሚችል ዘዴ ያዘጋጃሉ። ሹሞቹም ፤ የመፈንቅለ -መንግግሥት ( ኩዴታ ) ተፈጥሮ አከሸፍነው የሚል ቲያትር ቢያሳዩም ቅሉ፤ ሕዝብ ግን፤ ከቀልድ በስተቀር ምንም ዜጋ እንደ ዕውነት አልወሰደላቸውም ። አላመናቸውም ።ይልቁንም ፤ "መንግሥትን ማመን ቀብሮ ነው ! " የሚለውን ይትበሃል አጠንክሮለታል። ሹሙ ወደ ሥልጣን በመጣበት አካባቢ በተናገረው ማማለያ ሳቢያ፤ ሕዝቡ ግብታዊ ይሁንታ ያሳየው መሆኑ ባይካድም፤ ዉሎ -አድሮ የነገሮቹን አካሄድ ከተገነዘበ በኋላ ግን ከትዝብት አልፎ፤ "ዐይንህን -ለዐፈር " ብሎታል። ነቅቶበታል፤ያው ዘረኛ ወንጀለኛ መሆኑን አውቋል ።

በአንድ ዐመት የአፍላ ወራት ብዙ ተብሏል። ተሰምቷል። ታይቷልም። ጥቂት የማይባሉ ሁኔታዎች ተለዋውጠዋል። የሕዝቡም ተስፋ ተመንጥቆ ነበር ። ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያሸጋግረው መንገድ ግን፤ ለሕዝብ ዝግ ሆኖ ቆይቷል። የህዝብ ተሳትፎ እድል አላገኘውም። ሹሙ እኔ እራሴ አሸገግራችኋለሁ ብሎ የሕዝቡን ተሳትፎ በእምቢ ሸኝቷል። ዛሬ የተሰየሙብን ገዢዎች ጸረ ሀገር ጸረ ዴሞክራሲ መሆናቸው በማያጠራጥር ደረጃ ተርገጋጧል ማለት እንችላለን ።

ኢትዮጵያን ከዘረኞቹ ጥፋት ለማዳን በጋራ እንታገል ።

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች!
« Last Edit: August 02, 2019, 10:48:44 AM by staff3 »