የትግልን ስልት ወሳኝ ማን ነው?

የትግልን ስልት ወሳኝ ማን ነው?
የፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሀተታ ሐምሌ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. የተላለፈ

አንዳንዶች የትግልን ስልት ሊወስኑ የሚችሉት ምሁሮች ወይም የዘመናችን ዶክተር ደጃዝማቾች ናቸው ብለው ያምናሉ። ይህ ስህተት ነው ። ምሁሮች ነን ባዮቹ ራሳቸው በዚህ ስህተት ተዘፍቀው በዘፈቀደ ሰላማዊ ትግል በስተቀር ሌላ አማራጭ የለም ብለው ቁርጥ ያለና የተሳሳተ አቅዋም ይዘው መቆየታቸውን አስተውለናል ። ምን ዓይነት ትግል ሕዝብን ለድል ያበቃል ብሎ ወሳኙ ግን በስልጣን ላይ ያለው ገዢ መደብ ወይም ቡድን ነው ።

የሰፈነው ስርዓት የመወገጃውንም መንገድ ያረጋግጣል ። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከሰፈነና አፈና ከሌለ በሰላማዊ መንገድ፤ በምርጫ ወዘተ… ለውጥን ማጣት ይቻላል፤ ይለመዳልም ። የጭቆና አገዛዝ ከሰፈነና ሕዝብ ፍላጎቱን ሊሟላ ባልቻለበት፤ አገዛዙ አረመኔና ፋሺስታዊ ሆኖ በተሰየመበት ግን ሁኔታው የሚጠቁመውና የግድ የሚያደርገው አመጽን ነው ። ሁኔታው ግድ የሚለውን መገንዘብ ካቃተና ላም ባዋልበት ኩበት ለቀማ ከተገባ ጨቋኙ አገዛዝ ይበረክታል። መድፍ ሲገባው ጭቃ ይወረወርበታል ማለት ነው ። ገዢው ክፍል የሕዝብን መብት አክብሮ እስካልተገኘ፤ ለለውጥና መሻሻል ዝግ ሆኖ ክተገኘ፤ ደግሞ ደጋግሞ አፈና ሲያስፋፋ ምርጫን ሲያጭበረበር እየታየ ያለውን ሁኔታ አልረዳም በማለት በሰላማዊ ትግል ለውጥን መጠበቅ ጫንቃን ለባርነት ቀምበር ማመቻቸት ነው ።

ወያኔ ስልጣን እንደያዘ ተሯርጦ ሊያሰፍን የጣረው ሀሳብና አቅዋም ከእንግዲህ አመጽና እብረት ትግል አከተመ የሚለውን ነበር ። ይህን አደናጋሪና ትጥቅ አስፈቺ አቅዋም ዶክተር ደጃዝማቾች ደግፈው መላ ነው እንጂ ዱላ ተዉ ብለው ሲሰብኩና ሕዝብንም ሲያዘናጐለት ከረሙ ። የሕዝብ መብት ባልተከበረበት ግን ሰላም ሰላም የሚባልበት አልነበረም ። ስልጣን ሲይዝ ወያኔ ለዝቦና ለስልሶ ሳይሆን ዘረኛነቱንና አፋኘቱን አጠናክሮ እንደነበርም የሚታይ ነበር ። እስር ቤቶች እንዲሞሉ አድርጎ፤ በእጁ የወደቁትን ሁሉ መዳረሻቸውን አጥቶና ረሽኖ ፤ የተቹትንና የተቃወሙትን ለስየል ዳርጎ፤ ለብዙዎች ስደትን ሳይወዱ በግድ እንደአማራጭ አንዲይዙ አድርጎ ነበር ። በዚህ ወቅት የወያኔ ቅጥረኞችን አደናጋሪ ሰበካ አንሰማም ብለው ብረት አንስተው ወደ ትግል የገቡትን ቡድኖች ግን ወያኔ ብቻ ሳይሆን ዶክተር ደጃዝማቾች በአመጸኛነትና ጸረ ስላምነት በማወገዝና ትግሉን በማምከን ለወያኔ የተመቸ ሁኔታ ፈጥረውለት የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው። የሰላሙ ሙከራ ይኸው እስከዛሬ ወያኔ ምርጫ በሚሉት አዙሪት ከቶ በከንቱ እያሽከረከረ ባዶ አስቀርቷል ።ገዢው ክፍል ራሱ በሰላም እየቀለደ፤ በትግል ክሆነም ሞክሩኝ ብሎ እየደነፋ፤ ታግለን ያገኝነውን በትግል ንጠቁን የሚል መፈክር እያሰማ የቆየ በመሆኑ አቋሙ ድብቅ አልነበረም ። ስልጣን ነጠቃው በአመጽ እንደሚሆን ጠቁሞናል ማለት ይቻላል ። በመሆኑም ሁለገብ ትግል ማካሄድ፤ ይህን መሰል የትግል ስልትን ማስቀደም ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የተወሰን ነው ማለት ትክክል ይሆናል ።

ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንዲሉ ወያኔን በሰላማዊ ትግል ብቻ መጋተር ይቻላል፤ይገባል ብሎ መቆሙ ስህተት መሆኑ የ1997 ኡ ግድያ ሳይሆን 24 ዓመታት ሙሉ ሲካሄድ የባጀው ግፍና ፍጅት የሚያረጋግጠው ነው ። ወያኔና ዴሞክራሲ፤

ወያኔና ሰላም፤ ወያኔና ፍትህ ተዋውቀው የማያውቁ በመሆናቸው ፤ዱባና ቅል ለየቅል በመሆናቸው ወያኔን በማይገባው የሰላም ቋንቋ ማነጋገሩ ፋይዳ ቢስ ነው ። 24 ዓመታት ሙሉም አይተነዋል ምንም–ከቶም ቅንጣትም–ለሕዝብ እንደማይጠቅም ። ከተመክሮ መማር ጊዜ በመፍጀቱ እነሆ ኢትዮጵያ ትደማለች፤ህዝቧም መከራና ግፍን ተቀባይ ሆኖ ይገኛል። በየአምስት ዓመቱ ምርጫ የሚባለውን የሞኝ ጨዋታ መጠበቁ አላከትም ብሎ ሕዝብን ከሚፈለገው ትግል አርቆ መገኘቱ ሀገርን ጎድቷል ። ወያኔ ሊቃወሙ ሊታገሉ የሚፈልጉትን በጸረ ሰላምነት ፈርጆ የሚያጠቃውም አለምክንያት አይደለም ።የሚያሳዝነው ይህን ማደናገሪያ ተቀብለው በሰላም ብቻ እንጂ በወያኔ ላይ ማመጹ ጎጂ ነው ብለው የሚለፍፉ ተቃዋሚ በሉን ባዮች ትምህርት አለመውሰዳቸው ነው ። በብረትና በአመጽ የመጣ በግድ ጨቋኝ ይሆናል የሚለውን መሰረተ ቢስ መደምደሚያ ማስተጋባታቸው አልቀረም ። የአሜሪካ ነጻነት የተረጋገጠው በአመጽና በአብዮት ነው ። በአያሌ ሀገሮች ዴሞክራሲ የተገኘችው ሕዝብ በአመጽ ተነስቶ፤ብረት አንግቦ ታግሎ ነው ። ይህ ነው ሀቁ ። በአንጻሩ ተለምኖ፤ አዝኖ ወይም የሕዝብን ጩኸት ሰምቶ ስልጣን የለቀቀ ጨቋኝ ሀይል ግን ተፈልጎ የሚገኝ አይደለም ። ሁለገብ ትግል አማራጭ የለሽ የትግል ጎዳና ነው ማለት ተገቢ ነው ። በሌላ ስምሪት ጊዜንም ህይወትንም ማባከን የሚመረጥ አይደለም ። ያለፉት 24 ዓመታት የወያኔ ጨቋኝ አገዛዝ አምጹ ተነሱ በሁሉም መስክ ወያኔን ተዋጉ የሚል ነው እንጂ ሌላ መልዕክት የለውም ።

http://ethfreedomfighter.blogspot.no/2015/07/blog-post_20.html